Search

"7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅ የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል እያደረገ ያለውን ተግባር አጠናክሮ ይቀጥላል" – ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

ቅዳሜ ግንቦት 22, 2018 54

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፣ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅ በሰው ኃይል፣ በትጥቅና በቴክኖሎጂ ያደረገውን ቅድመ ዝግጅት አስመልክቶ በዋና መስሪያ ቤቱ በተዘጋጀው ፕሮግራም ላይ ለጋራ ግብረ-ኃይሉ ማብራሪያ ሰጥቷል።

የኢ... ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እንደገለጹት፣ የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ ለምርጫው ያደረገው ዝግጅት እጅግ ጠንካራ ነው። ምርጫውን ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች የተለያዩ ሙከራዎችን እያደረጉ ቢሆንም፣ መከላከያ ሠራዊት ከሌሎች የፀጥታና ደኅንነት ኃይሎች እነዚህን የጥፋት ዕቅዶች ማክሸፉን አረጋግጠዋል።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አክለውም፣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከሪፎርሙ በኋላ በሰለጠነ የሰው ኃይል፣ በዘመናዊ ትጥቅና በቴክኖሎጂ መደራጀቱ የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅና በተለይም 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጠቅላይ አዛዥ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በበኩላቸው፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተቋቋመው የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር መረጃዎችን በመለዋወጥ እና ከህዝቡ ጋር በመተባበር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህም በቅድመ-ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ሂደት፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች እና የምርጫ ቁሳቁስ ስርጭት ደህንነት በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን አስታውቀዋል።

ኮሚሽነር ጀነራሉ አያይዘውም፣ ቀሪውን የምርጫ ሂደት ሰላማዊነት ለማረጋገጥ አስፈላጊ የሆኑ ሎጀስቲክስ እና ትጥቆች መሟላታቸውን እንዲሁም ለተልዕኮው የሚመጥን በቂ ስልጠና እና ኦሪንቴሽን የወሰደ የሰው ኃይል በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች መሰማራቱን ገልጸዋል።

በቀጣይም ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በቴክኖሎጂ የታገዘ የፀጥታና ደህንነት የማስከበር ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እና ከምርጫው በኋላ የሚከናወኑ ሂደቶችም በስኬት እንዲጠናቀቁ ግብረ-ኃይሉ ሙሉ ዝግጅት ማድረጉን ኮሚሽነር ጀነራሉ አረጋግጠዋል።