Search

ምርጫው የኢትዮጵያ አሸናፊነት የተረጋገጠበት ነው፦ የአዲስ አበባ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት

ማክሰኞ ግንቦት 25, 2018 127

የአዲስ አበባ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የድምፅ አሰጣጥ ሂደትን መጠናቀቁን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

ምርጫው ከቅድመ ዝግጅት ጀምሮ ግልጽነት እና ፍትሐዊነት የተንጸባረቀበት፣ በመራጩ ሕዝብና በተፎካካሪ ፓርቲዎች ዘንድ ከፍተኛ ቅቡልነት ያገኘ መሆኑን በመግለጫው አስታውቋል።

ምክር ቤቱ በመግለጫው እንዳመለከተው ግንቦት 24 ቀን 2018 . የተካሄደው ይህ ምርጫ መንግሥት በከተማዋ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ላይ ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር ያሳየበትና የኢትዮጵያ አሸናፊነት የተረጋገጠበት ሌላኛው ታሪካዊ ምዕራፍ ሆኖ አልፏል።

ከእነዚህም መካከል እንደ ትልቅ ጅምር የሚወሰደው የዲጂታል የእጩዎች ምዝገባ ሒደት አላስፈላጊ መጉላላትን የቀነሰ እና የእጩዎችን መረጃ እና ደኅንነት ያረጋገጠ የአሰራ ግልፅነትን የፈጠረ መሆኑ በምርጫው ሂደት ከታዩ ዐበይት አዎንታዊ ሁነቶች መካከል እንደሆነ ተመላክቷል።

በምርጫው ዕለት መላው የከተማዋ ነዋሪዎች ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ ያለምንም ቀስቃሽ በነቂስ በመውጣት ድምፅ መስጠታቸውን የገለጸው ምክር ቤቱ፣ በተለይም ሴቶች፣ ወጣቶች እና አረጋውያን ያሳዩት ከፍተኛ ተነሳሽነት ሂደቱን ይበልጥ እንዳደመቀው አብራርቷል።

ከምርጫ ጣቢያዎች የሚመጡ የአሠራር ችግሮችን በጋራ በመገምገም፣ ከምርጫ ቦርድ እና ከከተማው አመራሮች ጋር በቀጥታ በመነጋገር አፋጣኝ የእርምት እርምጃ መወሰዱ በፓርቲዎች እና በአስፈፃሚ አካላት መካከል መተማመንን ማጎልበቱ ተገልጿል። 

በተጨማሪም የከተማዋ የጸጥታ አካላት ያለምንም ወገንተኝነት፣ ፍጹም ገለልተኛ በሆነ መንገድ የምርጫ ጣቢያዎችን እና የመራጩን ሕዝብ ደኅንነት በመጠበቅ ላበረከቱት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ምክር ቤቱ ምስጋና አቅርቧል። 

በሂደቱም ምንም ዓይነት የጸጥታ መደፍረስም ሆነ የምርጫ ሕግ መጣስ ሳይኖር መጠናቀቁ የከተማዋን ነዋሪዎችና የጸጥታ አካላት ከፍተኛ የበስለት ደረጃ ያሳየ "የአዲስ አበባ ሞዴል" መሆኑ ተነግሯል።

የድምፅ መስጠት ሂደቱ በስኬት ተጠናቅቆ ወደ ቀጣዩ የድምፅ ቆጠራ እና ውጤት ማደራጀት ምዕራፍ መሸጋገሩን የጠቀሰው ምክር ቤቱ፤ የምርጫ ቦርድ ሕጋዊ አሠራርን መሠረት አድርጎ የከተማውን ውጤት በኦፊሴላዊ መልኩ እስኪገልጽ ድረስ መላው የከተማዋ ነዋሪዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት እና ደጋፊዎች ፍጹም በሆነ ትዕግሥት እንዲጠብቁ ጥሪ አቅርቧል።

በንፍታሌም እንግዳወርቅ