ዛሬ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የዓለም አካባቢ ጥበቃ ቀንን እያከበረ ይገኛል። የዘንድሮው በዓል በአዘርባጃን ሪፐብሊክ ዋና አስተናጋጅነት ባኩ ከተማ "በተፈጥሮ አነሣሽነት፣ ለአየር ንብረት፣ ለነገው ሕልውናችን" በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ነው።
ዓለም አቀፉ ዘመቻም "ለአየር ንብረት እርምጃ አሁኑኑ" በሚል መሪ ቃል እየተመራ ይገኛል። ምድራችን እጅግ የበረቱ የአየር ንብረት መዛባት ምልክቶችን እያሳየች ባለችበት በዚህ ወሳኝ ወቅት ኢትዮጵያ ለችግሩ ምላሽ የሚሰጡ ግዙፍ ተግባራዊ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ትገኛለች።
የዘንድሮው የዓለም አካባቢ ጥበቃ ቀን አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ እውነታዎች
የዘንድሮው በዓል የሚከበረው የዓለም የአየር ንብረት መዛባት በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ መምጣቱን ሳይንሳዊ መረጃዎች በሚያሳዩበት ወቅት ነው።
እ.አ.አ ከ2015 እስከ 2025 የነበሩት 11 ዓመታት በዓለም ታሪክ ውስጥ እጅግ ሞቃታማ ዓመታት ሆነው ተመዝግበዋል።
በባኩ እየተካሄደ ባለው ዝግጅት ላይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝን ጨምሮ በርካታ ዓለም አቀፍ መሪዎች መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የአፍሪካ ኅብረት የ2026 ዓመትን ዘላቂ የውኃ አቅርቦት እና አስተማማኝ የንፅህና አጠባበቅ ሥርዓቶችን ለማረጋገጥ ትኩረት የሰጠበት መሪ ቃል የአህጉሪቱን የአየር ንብረት መቋቋም አቅም ለማሳደግ ያለመ ነው።
ይህ አህጉራዊ ንቅናቄ ኢትዮጵያ ከምትከተለው ፖሊሲ ጋር ቀጥተኛ ትሥሥር ያለው መሆኑ የሀገራችንን ስልታዊ ትክክለኛነት ያረጋግጣል።
የኢትዮጵያ ልዩ ትኩረት እና ታሪካዊው የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እና የሥነ-ምኅዳር መራቆትን ለመቀልበስ ከወሰደቻቸው እርምጃዎች መካከል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት በ2011 ዓ.ም የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ግንባር ቀደሙን ስፍራ ይይዛል።
ይህ ታላቅ ሀገራዊ ንቅናቄ በዓለም ላይ ካሉት ትልልቅ የደን መልሶ ማልማት ሥራዎች አንዱ ሆኖ ተመዝግቧል። መርሐ ግብሩ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል።
በዚህ ዓመት መርሐ ግብሩ ስምንት ዓመት የሚሆነው ሲሆን፣ አጠቃላይ የተተከሉትን ችግኞች ቁጥር ከ54 ቢሊዮን ለማድረስ ግብ ተቀምጦ እየተሠራ ነው።
ይህ ከፍተኛ ሀገራዊ ጥረት የኢትዮጵያን የደን ሽፋን በአስደናቂ ሁኔታ በ2010 ከነበረበት 17.2 በመቶ ወደ 23.6 በመቶ ከፍ እንዲል አድርጎታል።
ይህም ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ጥበቃ በተግባር ያስመሰከረችበት ቁርጠኝነት የሚያሳይ ለውጥ እያመጣ ይገኛል።
ከሀገር አቀፍ የላስቲክ እገዳ እስከ ዘላቂ የኢኮኖሚ ሽግግር
ሌላኛው የኢትዮጵያ አስደናቂ የአካባቢ ጥበቃ እርምጃ በአንድ ጊዜ አገልግሎት ላይ በሚውሉ የላስቲክ ከረጢቶች ላይ የተጣለው ሙሉ እገዳ ነው።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ባፀደቀው የደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር እና አወጋገድ አዋጅ ቁጥር 1383/2017 መሠረት በሀገር አቀፍ ደረጃ የአንድ ጊዜ አገልግሎት የሚሰጡ የላስቲክ ከረጢቶች ምርት፣ ሽያጭ እና አጠቃቀም ሙሉ በሙሉ ተከልክሏል።
ይህ እገዳ የአፈር እና የውኃ ብክለትን ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ሲሆን፣ በአማራጭነት የወረቀት እና የሸራ ከረጢት አምራች ወጣት ሥራ ፈጣሪዎችን በማነቃቃት አዳዲስ የኢኮኖሚ እድሎችን እየፈጠረ ይገኛል።
ከዚህም ባሻገር፣ ሀገራችን በየዓመቱ ለነዳጅ የምታወጣውን 5 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ወጪ ለመቀነስ እና የአየር ብክለትን ለመግታት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በማስፋፋት ላይ ሰፊ ትኩረት አድርጋለች ።
ቀጣናዊ ተፅዕኖ እና የ"አረንጓዴ ወንድማማችነት" ትሥሥር
የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ጥረት በሀገር ውስጥ ብቻ የተገደበ ሳይሆን ቀጣናዊ እና አህጉራዊ ፋይዳው እጅግ እየጎላ መጥቷል።
በ"አረንጓዴ ወንድማማችነት" መርሕ መሠረት ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት ለምሳሌ ለጅቡቲ እና ለደቡብ ሱዳን ሁለገብ ጥቅሞች ያሏቸውን ችግኞች እያቀረበች ትገኛለች።
የናይጄሪያ ምክትል ፕሬዝዳንት ካሺም ሸቲማን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ መሪዎች የኢትዮጵያን አረንጓዴ አሻራ ተሞክሮ ለአፍሪካ አህጉር ስልታዊ አርአያ ሲሉ አወድሰውታል።
የአፍሪካ ኅብረትም ይህንን የኢትዮጵያ ጥረት የምድረ-በዳነት መስፋፋትን ለመከላከል ለሚደረገው የአህጉሪቱ የታላቁ አረንጓዴ ግንብ ተነሣሽነት ትልቅ ደጋፊ አድርጎ ይመለከተዋል፡፡
በለሚ ታደሰ