Search

የኢትዮጵያ ሃይማኖታዊ ቅርሶች ወደ አገር ቤት ተመለሱ

ዓርብ ግንቦት 28, 2018 52

የሮም ነዋሪ የሆኑ ሎሬንዞ ቦሲ የተባሉ ግለሰብ ከበርካታ ዓመታት በፊት በሟች አባታቸው የተሰባሰቡ የኢትዮጵያ የዕጅ ጥበብ የሆኑ 18 ታሪካዊ መስቀሎች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ በከተማዋ ለሚገኘው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ኤምባሲ አስረክበዋል።
በጣሊያን የኢፌዴሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ደሚቱ ሀምቢሳ፣ ቅርሶቹ ወደ ኢትዮጵያ በይፋ እንዲመለሱ ላደረጉት ለሎሬንዞ ቦሲ እና አጋሮቻቸው ምስጋና በማቅረብ ለግለሰቡ የምስጋና የምስክር ወረቀት ማበርከታቸውን የቱሪዝም ሚኒስቴር ገልጿል።
በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት የሎሬንዞ ቦሲ አባት ኤንሪኮ ቦሲ በሕይወት ዘመናቸው የኢትዮጵያን ቅርሶች ሲያሰባስቡ የነበሩ እንዲሁም በኢትዮጵያ ታሪክና ባህል ዙሪያም ከ20 በላይ መፃሕፍትን ያሳተሙ መሆኑን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ገልጿል።
ቅርሶቹ ሮም ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ወደ ሀገራችን የሚጓጓዙበትን መንገድና ሂደት በቀጣይ ከኤምባሲው ጋር በመነጋገር እንደሚመቻች ባለስልጣኑ አስታውቋል።
በርክክቡ ላይ በጣሊያን ተቀማጭ የሆኑ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ተወካዮችና በሮም የኢትዮጵያውያን ዳያስፖራ ማህበረሰብ ተወካዮች የተገኙ ሲሆን፣ በዚሁ ወቅት የኢትዮጵያ ታሪካዊ ቅርስ ወደ አገሩ መመለሱ እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል።