Search

ኢትዮጵያ ዐይኗን ከባሕር በር አጀንዳዋ አትነቅልም

ዓርብ ግንቦት 28, 2018 57

ባለፉት አምስት ዓመታት የዓለማችን የጂኦ-ፖለቲካ መልክዓ ምድር አዲስ መልክ እየያዘ፣ የኃያላን ሀገራት የኃይል ሚዛን ከነጠላ የበላይነት ወደ ብዝኃ-ዋልታ ሥርዓት በፍጥነት እየተሸጋገረ ይገኛል።

በተለይም ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ማግስት ጀምሮ እስከ ሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት፣ እንዲሁም በቅርቡ በመካከለኛው ምሥራቅ የተከሰቱት ውጥረቶች ዓለም አቀፉን የንግድ እና የደኅንነት ሥነ ሥርዓት ክፉኛ አናግተውታል።

ይህ የዓለም አቀፍ የኃይል ሽግሽግ እና ትንቅንቅ፣ እንደ ቀይ ባሕር፣ የባብ ኤል-ማንደብ እና የኤደን ባሕረ ሰላጤ ያሉ ስትራቴጂያዊ የውኃ ማነቆዎችን የአዲሱ ጂኦ-ፖለቲካዊ ፉክክር ማዕከል አድርጓቸዋል።

በዚህ ወሳኝ የውኃ መስመር ላይ የበላይነትን ለመቀዳጀት፣ ነባር ኃያላን መንግሥታትም ሆኑ በቀጣናው ብቅ ያሉ አዳዲስ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ኃይሎች የባሕር ኃይል ጦር ሰፈሮቻቸውን ለማስፋፋት ከፍተኛ እሽቅድምድም ይዘዋል።

በቀይ ባሕር ቀጣና የሚታየው ይህ የወታደራዊ ኃይሎች ክምችት፣ የጥምረቶች መፈጠር እና መፍረስ፣ እንዲሁም የዲፕሎማሲያዊ ሽኩቻ የሚያሳየው አንድ ዐቢይ እውነት አለ።

ይኸውም፣ የዘመናችን የብሔራዊ ደኅንነት፣ የኢኮኖሚ ሕልውና እና የፖለቲካ ሉዓላዊነት በቀጥታ ከባሕር በሮች እና ከውኃ ላይ ጂኦ-ፖለቲካዊ ተደራሽነት ጋር በጥብቅ የተቆራኘ መሆኑን ነው። የዓለም የንግድ መስመር በተንገዳገደ ቁጥር የየሀገራቱ የውስጥ ኢኮኖሚ እና መረጋጋት በቀጥታ ይፈተናል።

በዚህ እጅግ ወሳኝ እና ፈታኝ ቀጣና ውስጥ፣ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድ አንኳር ሀገር ነች። 130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት፣ በፍጥነት እያደገ ያለ ኢኮኖሚ የምታስተዳድር እና ታሪካዊ የጂኦ-ፖለቲካዊ ክብደት ያላት ታላቅ ሀገር፣ ከባሕር በር ርቃ መታፈኗ የዘመናችን ትልቁ የፖለቲካዊ ተቃርኖ ነው።

አንኳር ሀገር ሆኖ ያለ የባሕር በር መገኘት፣ ልክ ግዙፍ ሳንባ ይዞ አየር እንደማጣት ይቆጠራል። በቀጣናው ያለው የፖለቲካ እና የፀጥታ ተለዋዋጭነት እያየለ በመጣበት በዚህ ዘመን፣ ኢትዮጵያን የመሰለች ግዙፍ ሀገር የደኅንነት እና የኢኮኖሚ ሉዓላዊነቷን በሌሎች ሀገራት በጎ ፈቃድ ላይ ብቻ ማንጠልጠል አትችልም።

ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶቻችን፣ ሰፋፊ የኢንዱስትሪ ፓርኮቻችን፣ ብሔራዊ የዕድገት ግቦቻችን እና እያደገ የመጣው የማምረት አቅማችን በሙሉ አስተማማኝ፣ የማይቋረጥ እና በራስ ቁጥጥር ሥር ያለ የሎጂስቲክስ እና የባሕር ትራንስፖርት መስመርን ይሻላሉ።

ባለፉት አምስት ዓመታት በቀጣናው የታዩት የውክልና ጦርነቶች፣ የባሕር ላይ ትራንስፖርት መስተጓጎሎች እና የኃይሎች ሰልፍ፣ የባሕር በር ማግኘት ለኢትዮጵያ የቅንጦት ጥያቄ ሳይሆን፣ ብሔራዊ ደኅንነትን፣ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን፣ የሕዝብን የምግብ ዋስትና እና የቀጣናዊ ሰላምን የማረጋገጥ የሕልውና ጉዳይ መሆኑን በግልጽ አሳይተዋል።

በተጨማሪም፣ የቀጣናውን ጂኦ-ፖለቲካዊ ሚዛን ለማስጠበቅ የኢትዮጵያ በባሕር በር ላይ መገኘት ወሳኝ ነው። ኢትዮጵያ ከባሕር በራቀች ቁጥር፣ የቀጣናው የፖለቲካ ስበት በውጭ ኃይሎች እጅ እንዲወድቅ እና የአፍሪካ ቀንድ የባዕዳን መፈንጫ እንዲሆን በር ይከፍታል።

ኢትዮጵያ እንደ አንኳር ሀገር፣ የገዛ ደኅንነቷን በማስከበር የቀጣናውን ሰላም ለማረጋገጥ በቀይ ባሕር ላይ የራሷ የሆነ ስትራቴጂያዊ እና የንግድ ወደብ፣ እንዲሁም ይህንን የሚጠብቅ ጠንካራ የባሕር ኃይል መኖሩ የግድ ይላታል።

ይህንን ተፈጥሯዊ እና ታሪካዊ መብት ለማረጋገጥ፣ ኢትዮጵያ የምታደርገው ጥረት፣ መሬት ላይ ያለው ጂኦ-ፖለቲካዊ እውነት የቱንም ያህል ውጣ ውረድ ቢኖረውም፣ አንዳንዶች በስጋት ቢመለከቱትም፣ ኢትዮጵያ ታሪካዊ ስህተቶችን አርማ፣ ዘላቂ የልጆቿን ደኅንነት ለማስጠበቅ ወደ ተፈጥሯዊ የባሕር ርስቷ ለመመለስ የጀመረችውን ሕጋዊ እና ሰላማዊ ጉዞ አታቋርጥም።

ማዕበልን ፈርቶ ከጉዞ የሚቀር መርከብ እንደሌለ ሁሉ፣ የቀጣናውን ውስብስብ የፖለቲካ ሽግሽግ እና የኃይሎች ፉክክር አይታ፣ የባዕድ እና ባንዳ ተልዕኮ እና ከንቱ ሙከራዎች ምክንያት ኢትዮጵያ ከስትራቴጂያዊ እና ታሪካዊ ግቧ አታፈገፍግም።

የአፍሪካ ቀንድ ዋልታ የሆነችው ሀገራችን ዘላቂ ሰላም፣ ደኅንነት እና ብልጽግና የሚረጋገጠው በመሬት ላይ ባላት ጠንካራ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መሠረት ብቻ ሳይሆን፣ በውኃ ላይም ተገቢውን ስፍራ ስትይዝ ነው። ለዚህም ነው፣ የቱንም ያህል ፈተናዎች ቢበዙ፣ ጂኦ-ፖለቲካዊ ንፋሶች በተለያየ አቅጣጫ ቢነፍሱም፣ ኢትዮጵያ ዐይኗን ከባሕር በር ላይ አትነቅልም የምንለው።

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ