Search

በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ደንበኞች የባንክ ሒሳብን ከፋይዳ መታወቂያ ጋር ማጣመርን በተመለከተ ከንግድ ባንክ የተሰጠ መግለጫ

ዓርብ ግንቦት 28, 2018 41

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባወጣው መመሪያ መሠረት በዋና ዋና ከተሞች በሚገኙ የባንካችን ቅርንጫፎች የተከፈቱ የባንክ ሒሳቦች ባለቤቶች የሆኑ እና እስከ ግንቦት 6 ቀን 2018 . ከፋይዳ መታወቂያ ጋር ሳያጣምሩ የቀሩ ደንበኞች በቀጣይ እስኪያጣምሩ ሒሳባቸው በጊዜያዊነት እንዳይንቀሳቀስ መደረጉ ይታወቃል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መኖሪያቸውን ከኢትዮጵያ ውጭ ያደረጉ ደንበኞች የባንክ ሒሳባቸውን ከፋይዳ መታወቂያ ጋር ማጣመር ሳያስፈልጋቸው በጊዜያዊነት በልዩ ሁኔታ መስተናገድ የሚችሉበትን አሠራር ዘርግቷል።

በዚህ መሠረት ከዚህ በፊት ሒሳብ በሚከፍቱበት ወቅት የመኖሪያ አድራሻቸው ከኢትዮጵያ ውጭ እንደሆነ በባንካችን የመረጃ ቋት የተመዘገበ ማስረጃ ያቀረቡ ደንበኞች ሒሳብ ያልታገደ መሆኑን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስታውቋል።

በተለያየ ምክንያት ውጭ ሀገር እንደሚኖሩ በባንኩ የመረጃ ቋት ላይ ያላስመዘገቡ እና የባንክ ሒሳባቸው የታገደባቸው ደንበኞች ከዚህ በታች በተገለፀው አግባብ መስተናገድ የሚችሉ መሆኑን ገልጿል፦

1. ከኢትዮጵያ ውጭ መኖራቸውን የሚገልፅ ማስረጃ ለምሳሌ - የትምህርት ማስረጃ፣ የሕክምና ማስረጃ፣ የውጭ ሀገር መንጃ ፈቃድ፣ ከውጭ ሀገር የተሰጠ ውክልና፣ የመኖሪያ ፈቃድ (የሎው ካርድ) የሥራ ፈቃድ ወይም ሀገር ውስጥ እያሉ የተሰጠ ውክልና ሆኖ ነገር ግን ውክልናው ላይ ውጭ ሀገር መኖራቸውን የሚገልጽ ሐሳብ ካለ በሕጋዊ መኪሎቻቸው አማካኝነት በማቅረብ እግዱን ማስለቀቅ ይችላሉ፤

2. ዲፕሎማቶች የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ መታወቂያቸውን በማሳየት ወይም ሒሳቡ የተከፈተው በዲፕሎማት መታወቂያ ከሆነ እግዱ ተነስቶላቸው ሒሳባቸውን ማንቀሳቀስ ይችላሉ፤

3. ደንበኛው በውጭ ሀገር እንደሚኖር የሚያረጋግጥ የኢሜይል መልእክት በኢምባሲ/ቆንስላ በኩል ከመጣ እግዱ በጊዜያዊነት ተነስቶላቸው መሰተናገድ ይችላሉ፤

4. በተጨማሪም ደንበኞች በውጭ ሀገር መኖራቸውን ሊያስረዱ የሚችሉ ማስረጃዎችን በቀጥታ የባንክ ሒሳቡ በተከፈተበት ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ የኢ-ሜል አድራሻ ወይም በዲያስፖራ ባንኪንግ ክፍል የኢ-ሜል አድራሻ DiasporaBanking@cbe.com.et በመላክ እግዱን በጊዜያዊነት ማስነሳት ይችላሉ ብሏል የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ።