ኢትዮጵያ በበርካታ ታሪካዊ፣ ባህላዊና ተፈጥሯዊ የቱሪዝም መዳረሻዎቿ የምትታወቅ ሀገር ብትሆንም፤ እስካሁን ድረስ በዓለም አቀፉ የክሩዝ (Cruise) ቱሪዝም ካርታ ውስጥ መካተት አልቻለችም።
በአንጻሩ በሜዲቴራኒያን፣ በካሪቢያን፣ በደቡብ ፓስፊክ እና በሰሜን አውሮፓ የሚገኙ ሀገራት ግዙፍ የመንገደኞች መርከቦችን (Cruises) በማስተናገድ ዓለም አቀፍ ቱሪስቶችን እየሳቡ ይገኛሉ። ኢትዮጵያ ግን የባህር በር ባለመኖሯ ምክንያት ከዚህ ዘርፍ ማግኘት የሚገባትን ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጥቅም ሳታገኝ ቆይታለች።
በአህጉራችን አፍሪካም እንደ ሲሼልስ፣ ሞሪሺየስ፣ ሞሮኮ፣ ኬንያ (ሞምባሳ) እና ደቡብ አፍሪካ (ኬፕታውን) ያሉ ሀገራት ባህርን መሰረት ያደረጉ የቱሪስት መዳረሻዎችን በማልማት የሀገር ውስጥና የዓለም አቀፍ ጎብኚዎችን ማዕከል መሆን ችለዋል።
እነዚህ ሀገራት የባህር በር ባለቤት መሆናቸው በቱሪዝም ዘርፍ ላይ ከፍተኛ መነቃቃትን በመፍጠር የሀገራቸውን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ እንዲያሳድጉ ረድቷቸዋል።
የባህር በር መኖር ለንግድ ማሳለጫነት ብቻ ሳይሆን ለሀገር ገጽታ ግንባታ እና ለዓለም አቀፍ ትኩረትም ያለው ሚናም የጎላ ነው።
በቱሪዝም ዘርፍ የሚፈጠር የባሕር በር ትስስር ሀገራት በጋራ እንዲለሙና የጋራ ጥቅማቸውን እንዲያረጋግጡ ሰፊ እድል ይፈጥራል።
የባህር በር ያላቸው ሀገራት በኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን በባህልና በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ጭምር ይበልጥ ተቀራርበው እንዲሰሩ ያደርጋል፤ በአሁኑ ወቅት ግማሽ ያህሉ የዓለም ቱሪዝም መዳረሻዎች በባህር ዳርቻዎች ላይ የተመሰረቱ በመሆኑም ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት ብትሆን በዘርፉ ያላትን ተወዳዳሪነት በከፍተኛ ደረጃ ታሳድጋለች።
የባህር በር መኖር ለዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት እና ለዓለም አቀፍ የቱሪዝም ተወዳዳሪነት እጅግ ወሳኝ ስፍራ የሚሰጠው ነው።
ስለሆነም ሀገራት የባህር በር ለማግኘት እና ያላቸውን የባህር ሀብት ለማልማት የሚያደርጉት ጥረት ተገቢ እና ወቅታዊ ተግባር መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው ።
በንፍታሌም እንግዳወርቅ