Search

አዲስ አበባን የአፍሪካ የከተሞች ልማት ተምሳሌት ያደረገው የ24/7 የመፈጸም አቅም

ዓርብ ግንቦት 28, 2018 65

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) ጥቅምት 12 ቀን 2016 . "የዛሬ አምስት ዓመት አዲስ አበባ በአፍሪካ ውስጥ እጅግ ውብ ከሚባሉ ከተሞች አንዷ ትሆናለች" በማለት አቅጣጫ ያስቀመጡት ከተማዋ ስሟን የምትመጥን እንድትሆን በማሰብ ነው።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል ዛሬ በከተማዋ ተግባራዊ በሆኑት መዋቅራዊ እና ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች አማካኝነት በተጨባጭ እውን እየሆነ ይገኛል።

ይህንን ታላቅ ሀገራዊ ራዕይ ወደ መሬት አውርዶ በተግባር ለመተርጎም ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያሳየው የአፈጻጸም ብቃት ሁነኛ ሚና ተጫውቷል።

በከንቲባ አዳነች አቤቤ የሚመራው የከተማዋ አመራር ቁርጠኝነት የለውጡ ዋነኛ አንቀሳቃሽ ሞተር ሆኖ አዲስ አበባን እንደ ስሟ የፈካች አበባ አድርጓታል።

አስተዳደሩ ያሰፈነው 24/7 (ቀን ከሌሊት) የሥራ ባህል ቀደም ሲል ለዘመናት ስር ሰድዶ የነበረውን ዝግተኛ የመንግሥት ቢሮክራሲ በመስበር፣ ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ እና በከፍተኛ ጥራት የማጠናቀቅ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ከፍቷል።

ይህ የሥራ ባህል ለውጥ ከተማዋን የማዘመን ተግባር ብቻ ሳይሆን፣ የከተማዋን ኢኮኖሚ ሌት ተቀን በማንቀሳቀስ ለበርካታ ዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል የፈጠረ የልማት ኃይል ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።

የአመራሩ በቢሮ ከመቀመጥ ይልቅ በምሽት የሥራ እንቅስቃሴዎች ላይ በአካል በመገኘት እና በመከታተል፣ በበዓላት ቀናት ከኮሪደር ልማት ሠራተኞች ጋር ማዕድ በመጋራት፣ እንዲሁም ሠራተኛውን በቅርበት በማበረታታት መሪነትን በተግባር አሳይተዋል።

ይህ ዓይነቱ ያልተቋረጠ የአመራር ክትትል እና አብሮነት የሥራ ባህልን በመቀየር ረገድ ትልቅ ሥነ-ልቦናዊ ለውጥ አምጥቷል።

የአስተዳደሩ ትጋት ከተማዋ ላይ ያመጣቸው ተጨባጭ ለውጦች ያፈሩት ፍሬ ዛሬ በገሃድ ይታያል፤ በርካቶችንም ተጠቃሚ አድርገዋል።

የከተማዋን ገጽታ ሙሉ ለሙሉ የቀየሩት ሰፋፊ የኮሪደር ልማቶች፣ ግዙፉ የዓድዋ ድል መታሰቢያ፣ የአዲስ አበባ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ሴንተር፣ የወንዝ ዳር ልማቶች፣ ማራኪ የሆኑት የሕዝብ መዝናኛ ስፍራዎች እና ዘመናዊ የመንገድ መሰረተ ልማቶች የአዲስ አበባን ትክክለኛ ውበት አጉልተው አውጥተውታል።

አዲስ አበባን የኪነ ጥበብ እና ፍልስፍና ማዕከል ለማድረግም ዘመናዊ የሲኒማ ኮምፕሌክሶች እና አምፊ ቴአትሮች በስፋት ተሠርተው ለአገልግሎት በቅተዋል።

አዲስ አበባ መጪውን ጊዜ ስታስብ ትላንቷንም ሳትረሳ ኢትዮጵያን ላገለገሉት ልጆቿ መታሰቢያ በማቆም ለቅርሶቿ ጥበቃ አድርጋለች።

የወንዝ ዳር ልማት፣ ትላንት የበሽታ እና የወንጀል ምንጮች የነበሩ ወንዞችን በማደስ ለከተማዋ አዲስ አስትንፋስ ሰጥቷል።

እነዚህ ተከታታይ ስኬቶች አዲስ አበባ ስሟን የሚመጥን ከተማ እንድትሆን ከማድረጋቸውም ባሻገር፣ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫነቷን እና የዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ማዕከልነቷን በሚመጥን መልኩ የዓለምን ቀልብ በከፍተኛ ሁኔታ እንድትስብ አድርጓታል።

ዛሬ ላይ ቱሪስቶችም ሆኑ ዓለም አቀፍ ልዑካን በከተማዋ ንጽህና እና ፈጣን ዕድገት መገረማቸውን በተደጋጋሚ ከመግለጽ አልፈው በአካል መጥተው ለዓለም አረጋግጠዋል።

መዲናችንን የጎበኙ ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ ፈጣሪዎችም ከተማዋ ከየትኛውም የዓለማችን ከተማ ጋር የምትወዳደር ውብ ከተማ እንደሆነች አረጋግጠዋል።

ከዚህም በላይ የከተማ አስተዳደሩ የጀመረው የኮሪደር ልማት እና የመልሶ ማልማት ሥራ፣ ማንንም ወደ ኋላ የማይተው ሰው-ተኮር መርሕን የተከተለ መሆኑ ልዩ ያደርገዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያስመዘገበው ይህ አስደናቂ የመፈጸም አቅም እና የልማት አርአያነት በዋና ከተማዋ ብቻ ተወስኖ አልቀረም።

ከተማ አስተዳደሩ ይህን ተጨባጭ ለውጥ ወደ ክልል ከተሞችም በተሳካ ሁኔታ እንዲሰርጽ አድርጓል።

ባለሙያዎችን በመመደብ እና የቴክኒክ ድጋፎችን በማቅረብ ታሪካዊቷ የጎንደር ከተማ የጀመረችውን የኮሪደር ልማት በፍጥነት እና በጥራት እንድታከናውን ትልቅ አሻራውን አሳርፏል።

በተመሳሳይ መልኩ የሐይቆች ከተማ የሆነችውን ቢሾፍቱ ከተማን የኮሪደር ልማት እና የቱሪስት መዳረሻነት ለማጠናከር የተደረጉት የልምድ ልውውጦች፣ የአመራሩን አጋርነት እና ሀገራዊ ቁርጠኝነት በተግባር ያሳዩ ናቸው።

በአዲስ አበባ የታየው ይህ አስደናቂ ለውጥ በምኞት የመጣ ሳይሆን፣ በጠንካራ መዋቅራዊ ዕቅድ፣ ቀን ከሌሊት በሚተጋ ቁርጠኛ አመራር፣ በተለወጠ የሥራ ባህል እና ከሕዝብ ጋር በተመሠረተ ጠንካራ ትሥሥር የመጣ ውጤት ነው።

ይህ ስኬት "የጀመርነውን እናጠናቅቃለን" የሚለውን የይቻላል መንፈስ በዜጎች ልቦና ውስጥ ያሰረጸ እና መላው ኢትዮጵያውያን በመዲናቸው እንዲኮሩ ያደረገ ብሩህ ተስፋ ነው።

አዲስ አበባ ዛሬ በአፍሪካ እጅግ ተወዳዳሪ፣ ለነዋሪዎቿ ምቹ እና ለሌሎች ከተሞች ታላቅ የልማት ትምህርት ቤት ሆና በኩራት ቆማለች።

በለሚ ታደሰ