Search

የመምህር ረዳት AI መተግበሪያ በሙከራ ደረጃ ሥራ ላይ ማዋሉን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ

ዓርብ ግንቦት 28, 2018 77

ትምህርት ሚኒስቴር የመምህራንን የዕለት ተዕለት የሥራ ጫና ለመቀነስ የተዘጋጀ ኤጀንቲክ መምህር ረዳት የተሰኘ የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) መተግበሪያን በሙከራ ደረጃ ሥራ ላይ አውሏል።

መተግበሪያው በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት መሠረት 9 እስከ 12 ክፍል ያሉ መጻሕፍትን በመረጃ ምንጭነት በመጠቀም የተገነባ ሲሆን፣ ኢንተርኔት ሳያስፈልገው በማንኛውም ኮምፒውተር ላይ ሊሰራ የሚችል እና የትምህርት እቅድ ማዘጋጀት፣ የፈተና ጥያቄዎችና አሳይመንቶች ማመንጨት እንዲሁም የማስተማሪያ ስልቶችን መጠቆም ይችላል ተብሏል።

የአይሲቲና ዲጂታል ትምህርት መሪ ሥራ አስፈጻሚ / ዘላለም አሰፋ እንዳሉት፣ ቴክኖሎጂው በክላውድ ወይም በማዕከላዊ ሰርቨር ላይ ሳይመረኮዝ በአካባቢያዊ ኮምፒውተር ላይ በቀላሉ የሚሰራ ሲሆን፣ ከፍተኛ የሃርድዌር አቅም አይፈልግም።

ይህ በተለይ የኢንተርኔት አገልግሎት ውስን በሆነባቸው የገጠር አካባቢዎች ላሉ ትምህርት ቤቶች አዲስ እድል እንደሚፈጥር ይገመታል። በተጨማሪም የኢንተርኔት ክፍያ፣ የክላውድ አገልግሎት ወጪ እና ሌሎች የመሠረተ ልማት ወጪዎችን በእጅጉ ይቀንሳል ተብሏል።

መተግበሪያው በተመረጡ ትምህርት ቤቶች በተደረገ ሙከራ አጥጋቢ ውጤት ማስመዝገቡን የገለጹት ኃላፊዎች፣ ከሁሉም ክልሎች ለተውጣጡ መምህራንና የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ስልጠና መሰጠቱንም ጠቁመዋል።

በዓለም ባንክ ድጋፍ በሚተገበረው ETOL ፕሮጀክት የሚደገፈው ይህ አዲስ AI ሥርዓት፣ የትምህርት ዘርፉን ዲጂታላይዜሽን ለማፋጠን እና የመምህራንን ሥራ ይበልጥ ቀላልና ውጤታማ ለማድረግ የሚረዳ እንደሆነ ተገልጿል።