7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በሰላማዊ ሁኔታ መጠናቀቁንና ታሪካዊ የህዝብ ቁርጠኝነት የታየበት መሆኑን የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ይፋ አድርጓል።
የፌዴሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር ገነት ስዩም በሰጡት መግለጫ፣ ሂደቱን በአገር አቀፍ ደረጃ በንቃት ለመታዘብ ከ14,000 በላይ ታዛቢዎችን በማሰማራት፣ 25,384 የምርጫ ጣቢያዎችን በስፋት ማዳረስ መቻሉን ገልጸዋል።
ፌዴሬሽኑ በምርጫው ላይ የሴቶች ተሳትፎ እጅግ አበረታች ደረጃ ላይ የደረሰ መሆኑን የገለጸ ሲሆን፣ ከተመዘገቡት ጠቅላላ መራጮች ውስጥ 49.3 በመቶው ሴቶች መሆናቸውን አረጋግጧል።
ከዚህም በተጨማሪ የሴት እጩዎች ቁጥር ከቀደሙት ምርጫዎች ጋር ሲነጻጸር በከፍተኛ ሁኔታ መሻሻሉን ዋና ዳይሬክተሯ ጠቁመዋል።
በአዲስ አበባ መራጮች የገጠማቸውን ፈተናዎች ተቋቁመው እስከ ሌሊቱ 6፡00 ሰዓት ድረስ በረጅም ሰልፍ ጠብቀው ድምጽ ለመስጠት ያሳዩት ትዕግሥትና ጽናት ለወደፊቱ የዴሞክራሲ ጉዞ ትልቅ ተስፋ የሰጠ መሆኑን ምስክርነቱን ሰጥቷል።
ከዚህ በተጨማሪ በአብዛኛዎቹ ጣቢያዎች ቆጠራው በግልጽነት መካሄዱ፤ የፓርቲ ተወካዮችና ታዛቢዎች በቆጠራ ውስጥ መሳተፋቸው በጥንካሬ ጎን ተነስቷል።
በአንዳንድ ጣቢያዎች ቆጠራ እስከ ማክሰኞ ድረስ መቀጠሉ፤ በሂደቱ ላይ የቴክኖሎጂው ሽግግር እና በአንዳንድ ጣቢያዎች የምርጫ አስፈጻሚዎች የግንዛቤ ክፍተት በሂደቱ ላይ ትልቅ ማነቆ ሆኖ ማለፉን ፌዴሬሽኑ አንስቷል።
የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ችግሮች በታዩበት ወቅት የወሰዳቸውን አፋጣኝ የእርምት እርምጃዎች እንዲሁም የጸጥታ አካላት ሂደቱ በሰላም እንዲጠናቀቅ በጥምረት ለሠሩት የጥንካሬ ሥራ በእጅጉ አድንቋል።
በቀጣይ ለሚካሄደው ምርጫ የዲጂታል አሠራር ሥርዓቱን ማዘመን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች በውስጥ አሠራራቸውና በመዋቅራቸው የሴት እጩዎችን ቁጥር ቢያንስ ወደ 30 በመቶ ለማሳደግ ቁርጠኛ እንዲሆኑ ምክረ ሀሳብ አቅርቧል።
በብሩክታዊት አሥራት