የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች በወልድያ ከተማ በከፍተኛ ፍጥነትና ጥራት እየተከናወኑ ያሉ ሰፊ የኮሪደር ልማት ሥራዎችን በምሽት ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል የከተማ ዘርፍ አስተባባሪ አሕመዲን መሐመድ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ወልድያ በርካታ ታሪካዊ ከተሞችን የምታገናኝ የንግድ መገናኛ ነች፡፡
አሁን እየተገነባ ያለው የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት የከተማዋን ስትራቴጂካዊ እሴት እና ተወዳዳሪነት በእጅጉ ከፍ አድርጎታል ብለዋል።
ቀደም ሲል ጎስቋላ እና ጠባብ ስፍራዎች ተወግደው፣ ምቹ ድልድዮች፣ ሰፋፊ የእግር መንገድ እንዲሁም ዘመናዊ የመዝናኛና የንግድ ቦታዎች መከፈታቸውን አብራርተዋል።
የኮሪደር ልማቱ ከውበት ማሻሻል ባለፈ የትውልድ እና የሀገር ግንባታ ጉዳይ መሆኑን ያነሱት አሕመዲን መሐመድ (ዶ/ር)፣ ዛሬ በእነዚህ ንጹሕ መንገዶች ላይ በነፃነት የሚንሸራሸሩ ሕፃናት ነገ ሀገርን በላቀ ሥነ ልቦና የሚረከቡ በመሆናቸው ሥራው ትውልድ ተሻጋሪ መሠረት ያለው መሆኑን አፅንኦት ሰጥተዋል።
በመሆኑም ሌሎች የክልሉ ከተሞች ከወልድያ ከተማ የፈጠራ አሠራር እና የሀብት ቁጠባ ልምድ ሊቀስሙ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።
የአማራ ክልል የከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ ሞላ መልካሙ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በአሁኑ ወቅት በክልሉ በሚገኙ 43 ከተሞች ውስጥ ማዘጋጃ ቤቶችን ጨምሮ የኮሪደር ልማት እንቅስቃሴ በተቀናጀ እና በሰፊ ሕዝባዊ ንቅናቄ እየተካሄደ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
ይህ ሀገር አቀፍ ተነሳሽነት የክልሉ ከተሞች ከዓመታት የተጎሳቆለ ገፅታ ተላቅቀው ምቹ የሥራ፣ የመኖሪያ እና የቱሪዝም ሥፍራ እንዲሆኑ እያደረገ ይገኛል።
ወልድያ ከተማ በውሱን የጊዜ ገደብ ውስጥ በጥራት በመሥራት አስደናቂ ለውጥ ማምጣቷን የጠቀሱት የቢሮ ኃላፊው፣ የከተማዋ አመራር ውስን ሀብትን በቁጠባ እና በጥራት የመጠቀም በአጭር ጊዜ የማሳካት ጥበብ መከተሉን አብራርተዋል፡፡
የወልድያ ከተማ አመራር እና ሕዝብ "ከተማችን ተጎሳቁላ አትኖርም" በሚል ጽኑ የጋራ መግባባት ፈጥረው፣ የውስጥ ሀብትን በብልሃት በማሰባሰብ እና ፈጣን እርምጃ በመውሰድ የከተማዋን ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ እሴት ከፍ አድርገዋል።
አመራሩ ከሕዝብ ጋር በቁርጠኝነት እና በተቀናጀ ሁኔታ ከተገጣጠመ ማንኛውንም የልማት እና የፋይናንስ ተግዳሮት ማሸነፍ እንደሚቻል ትልቅ ማረጋገጫ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
የወልዲያ ተሞክሮ ለአጠቃላይ ለክልሉ ከተሞች መነቃቃትን የሚፈጥር ታላቅ ትምህርት የሰጠ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።