ኢትዮጵያ በታሪኳ አያሌ የፖለቲካ ፈተናዎችን እና የውጭ ጫናዎችን በጽናት በመመከት የጀመረችውን ታላቅ ሕልም በድል የመጨረስ አኩሪ ታሪክ አላት።
በዚህ ዘመንም የሚደቀኑባትን ተስፋ አስቆራጭ ፈተናዎች አልፋ የታሪክ አቅጣጫዋን በራሷ ብቃት የመቀየር ያላሰለሰ ጉዞዋን አጠናክራ ቀጥላለች።
ይኸው ዛሬም የፈተናዎችን ማዕበል ተሻግራ ሁለንተናዊ ሰላም እና ዘላቂ መግባባትን ለማረጋገጥ ስታካሂድ የነበረችውን ታሪካዊ እና ትውልድ ተሻጋሪ ሀገራዊ ምክክር በስኬት አጠናቅቃለች።
ይህ የጽናት እና የራስ አቅም መገለጫ በፖለቲካው መስክ ብቻ ሳይወሰን በምግብ ራስን የመቻል ታላቅ ንቅናቄም በተግባር እየታየ ይገኛል።
በተለይም በበጋ ስንዴ ልማት፣ በክላስተር እርሻ እና በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብሮች የተመዘገቡት አስደናቂ ውጤቶች ኢትዮጵያ ከእጅ ወደ አፍ አሠራር ተላቅቃ የምግብ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ የምታደርገውን ጉዞ ያፋጠኑ ናቸው።
ከውጭ የሚገባን ስንዴ ማስቀረት ብቻ ሳይሆን ለውጭ ገበያ ማቅረብ መቻሏ፣ ኢትዮጵያውያን በራሳቸው መሬት እና ላብ ተአምር መፍጠር እንደሚችሉ ለዓለም ያስመሰከሩበት ሌላው የልማት ድል ነው።
ለዚህ የጽናት ጉዞ ሌላው ቁልፍ ማረጋገጫ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ነው። ኢትዮጵያውያን በየአቅጣጫው የመጣባቸውን የዲፕሎማሲ፣ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ጫናዎች በጋራ ክንዳቸው እና በራሳቸው አቅም መክተው ግድቡን ወደ ፍጻሜ ማድረስ ችለዋል።
ይህም ኢትዮጵያውያን ማንኛውም ፈተና ቢገጥማቸው ጀምረው የመጨረስ ተፈጥሯዊ ባሕሪያቸውን ለዓለም ያስመሰከሩበት ሕያው ምሳሌ ነው።
ልክ እንደ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሁሉ ኢትዮጵያ የራሷን የውስጥ ጉዳይ በራሷ ለመወሰን ልጆቿን በጠረጴዛ ዙሪያ የሚያሰባስብ ሀገራዊ ምክክር አዘጋጅታ በስኬት አጠናቅቃለች።
የምክክር ሒደቱን ለማክሸፍ በርካታ ፈተናዎች ተደጋግመው ቢመጡም፣ የኢትዮጵያውያንን የማይበገር አንድነት እና የጽናት መንፈስ ዳግም በማንሠራራት ሒደቱ ለስኬት በቅቷል።
ይህ እርምጃ የውስጥ ችግሮችን በውስጥ አቅም እና ዕውቀት የመፍታት ታላቅ መርሕን በተግባር ያረጋገጠ ነው።
ይህ ታሪካዊ የምክክር ሒደት የትናንት ቁስሎችን አክሞ፣ የጋራ ዕሴቶችን አጎልብቶ የነገዋን የበለጸገች፣ የተከበረች እና የታፈረች ኢትዮጵያን በጥብቅ መሠረት ላይ ለመገንባት የተጣለ ታላቅ የተስፋ መንገድ ነው።
ኢትዮጵያ በትናንትናው ታሪኳ በጽናት ስታሸንፍ የነበረች፣ ዛሬም ሁሉንም ፈተናዎች አልፋ እያሸነፈች ያለች፣ ነገም የታላቅነቷን ሕያው ምዕራፍ በደመቀ ቀለም የምትጽፍ ታላቅ ሀገር መሆኗን በእነዚህ ስኬቶች ዳግም ለዓለም አብስራለች።
በሔዋን ጌታቸው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: