Search

የቀጣናው ግርማ ሞገስ

ማክሰኞ ሰኔ 02, 2018 49

የአንዲት ሉዓላዊት ሀገር የጀርባ አጥንት፣ የሰላሟ ዋስትና እና የሕልውናዋ የመጨረሻው ምሽግ ጠንካራ፣ ዘመናዊ እና ለሕዝቧ ታማኝ የሆነ ብሔራዊ የመከላከያ ኃይል ነው።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በረጅም ዘመናት ታሪኩ በርካታ የጀግንነት ውጣ ውረዶችን ያሳለፈ እና አኩሪ ገድሎችን አስመዝግቧል፤ በቅርብ ዓመታት የተደረገው ጥልቅ እና ሁለንተናዊ የሪፎርም ሥራ ደግሞ ተቋሙን ወደ አዲስ የልዕልና እና የክብር ምዕራፍ አሸጋግሮታል።

የዚህ ታሪካዊ ሪፎርም ዋነኛ እና አንኳር ስኬት፣ ሠራዊቱን ከርዕዮተ ዓለም ጠባቂነት አላቅቆ የኢትዮጵያ እና የዜጎቿ የጋራ ክብር እና ደኅንነት ዘብ እንዲሆን ማድረግ መቻሉ ነው።

ባለፉት ዘመናት የፀጥታ እና መከላከያ ተቋማት የፖለቲካ ሥርዓቶች እና የገዢ ፓርቲዎች አገልጋይ ሆነው መቆየታቸው በተቋማቱ እና በሕዝቡ መካከል መተማመንን ሲሸረሽር ቆይቷል።

ይሁን እንጂ፣ በአዲሱ የለውጥ ጉዞ እነዚህ ተቋማት ሕገ መንግሥቱን ብቻ መሠረት አድርገው ሀገራዊ ተልዕኳቸውን እንዲያከናውኑ እና ከማንኛውም የፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ እንዲሆኑ ተደርገዋል።

የሕግ፣ የአሠራር እና የአደረጃጀት ሪፎርም በማድረግ ኢትዮጵያን የሚመጥኑ ተቋማት እንዲሆኑ የተደረገ ሲሆን፣ ይህ ስብራት መጠገኑ ሠራዊቱ የፖለቲካ ሥርዓት ሲቀየር አብሮ የሚፈርስ ሳይሆን፣ በገለልተኝነት እና በሙያዊነት እንዲሁም ራስን እና ሀገርን የሚያስቀጥል ጠንካራ ተቋም እንዲሆን አስችሎታል።

ከሥነ ልቦናዊ እና መዋቅራዊ ነፃነት ባሻገር፣ ሠራዊቱ ከኋላ ቀር አደረጃጀት እና የትጥቅ ሥርዓት ወጥቶ እጅግ ዘመናዊ ወደሆነ የውጊያ አቅም መሸጋገሩ ነው።

የፀጥታ እና የደኅንነት ተቋማትን ለማዘመን በተሠራው ሰፊ እና የተቀናጀ ሥራ፣ ሰብዓዊ፣ መዋቅራዊ እና ቴክኖሎጂያዊ ብቃት ያላቸው ጠንካራ ተቋማት ተፈጥረዋል። ዛሬ ላይ ተቋማቱ ዘመናዊ እና ዘመን ተሻጋሪ ሆነው በአዲስ መልክ በመደራጀታቸው፣ የሀገራችንን ሉዓላዊነት በአስተማማኝ ሁኔታ ለማስከበር የሚያስችል የላቀ ቁመና ተላብሰዋል።

በተጨማሪም፣ ዘመናዊ የመከላከያ ቴክኖሎጂዎችን በማላመድ እና በራስ አቅም በመፍጠር ረገድ የሀገርን አቅም በከፍተኛ ደረጃ እየገነቡ ይገኛሉ። ሠራዊቱ ለግዳጅ አፈጻጸም የሚያስፈልጉትን ትጥቆች እና ስንቆች በራስ አቅም ለማሟላት ዳር የደረሰ ሲሆን፣ በዚህም ኢትዮጵያን ከባንዳ እና ከባዕዳን ሴራ በአስተማማኝ ሁኔታ መከላከል ወደሚችልበት የማይበገር ደረጃ ላይ ደርሷል።

የመከላከያ ሠራዊቱ ልዕልና እና ሞገስ የሚለካው በዘመናዊ ትጥቁ እና በቴክኖሎጂው ምጥቀት ብቻ ሳይሆን፣ ለሕዝቡ ባለው ጥልቅ ፍቅር፣ የአደራ ጠባቂነት እና ሥነ ምግባር ጭምር ነው።

የኢትዮጵያ መከላከያ እና የፖሊስ ሠራዊት ዜጎችን ከማንኛውም እንግልት፣ ከመብት ጥሰት፣ ከሞት እና ከመፈናቀል አደጋ ለመታደግ ከፍተኛ የሕይወት መሥዋዕትነት በመክፈል ሌት ተቀን በግንባር ሲንቀሳቀስ ቆይቷል።

ዘመናዊ እና ዘመን ተሻጋሪ አድርጎ ከማደራጀት ባለፈ፣ ይህ ሪፎርም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በማሻሻል ረገድም አዎንታዊ ሚና እየተጫወተ ይገኛል። ይህን መሰል ሀገር ወዳድነት እና ለሕዝብ ደኅንነት የሚከፈል መሥዋዕትነት፣ ሠራዊቱ በመልካም ስሙ፣ በሕዝብ አክባሪነቱ እና በጀግንነቱ በሕዝቡ ዘንድ እጅግ የተወደደ እና የኩራት ምንጭ እንዲሆን አድርጎታል።

ሀገራችንን ከውስጥም ሆነ ከውጭ ከሚቃጡባት አደጋዎች ለመጠበቅ እና የሕዝባችንን ዘላቂ ደኅንነት ለማረጋገጥ ሠራዊቱን ይበልጥ ማጎልበት እና ማጠናከር ተችሏል።

ይህ ጽኑ ሥነ ምግባር ያለው እና በሙያዊ ብቃቱ የላቀው የኢትዮጵያ መከላከያ እና የፖሊስ ሠራዊት፣ የተሰጠውን ተልዕኮ እና ግዳጆቹን ሁሉ በአግባቡ በመፈጸም በቀጣናው ብሎም በዓለም ሰላምን የማምጣት እና የመጠበቅ ታላቅ ሚናውን በብቃት እየተወጣ ይገኛል።

ሠራዊታችን በሀገር ውስጥ የሕግ የበላይነትን እና ሉዓላዊነትን ከማስከበር ባለፈ፣ በአፍሪካ ቀንድ እና በአኅጉራዊ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ላይ የሚያሳየው ወደር የለሽ ጀግንነት እና የሰላም ዘብነት "የቀጣናው ግርማ ሞገስ" የሚለውን ከበሬታ በተግባር ያጎናጸፈው ነው።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ባለፉት የለውጥ ዓመታት ያካሄደው ጥልቅ እና ስኬታማ የሪፎርም ሥራ፣ ከፖለቲካዊ ወገንተኝነት ወደ ፍጹም ሕገ መንግሥታዊ ታማኝነት፣ እንዲሁም ከኋላ ቀር አደረጃጀት ወደ ዘመናዊ ቴክኖሎጂያዊ ልዕልና የተደረገ እውነተኛ የተቋም ትንሣኤ ማሳያ ነው።

ዛሬ ላይ በኩራት እንደምንመለከተው ሠራዊታችን የሕዝብ ደኅንነት አስተማማኝ ዋስትና፣ የሀገር ሉዓላዊነት የማይደፈር የመጨረሻው ምሽግ፣ እና ለዘመናት በክብር የምንጠራው የቀጣናው ግርማ ሞገስ ሆኖ በታላቅ ልዕልና ደምቆ ቆሟል።

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ