የአርባ ምንጭ ከተማ መሶብ አንድ ማዕከል በይፋ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት፣ የመደመር መንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል ቀዳሚ የትኩረት መስክ አድርጎ እየሠራ ይገኛል።
በክልሉ 2ኛ የሆነው አገልግሎት መስጫ ማዕከል ከዛሬ ጀምሮ በይፋ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ጠቅሰው፣ በማዕከሉ የሚሰጠው አገልግሎት ኃላፊነትን ከተጠያቂነት ጋር በማስፈን የአገልግሎት ጥራት እና ተደራሽነትን ለማሳደግ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ብለዋል።
አገልግሎቱ ሰው ተኮር ሥራዎች ላይ ከፍተኛ ለውጥ የሚያመጣ ሀገራዊ ኢኒሼቲቭ በመሆኑ፣ የክልሉ መንግሥት ጥራት እና ተደራሽነትን ማረጋገጥ ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ይሠራል ብለዋል።
የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አልማዝ መሠለ፣ መንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን ትኩረት ሰጥቶ በመሥራቱ እስካሁን በ11 ክልሎች 51 ማዕከላት ተከፍተው አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ሥራ ላይ ባሉ ማዕከላት ኅብረተሰቡ ጥቅሙን በአግባቡ ማጣጣም መጀመሩን ኮሚሽኑ አረጋግጧልም ብለዋል።
አስተያየታቸውን የሰጡ የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች በበኩላቸው፣ አገልግሎቱ በመጀመሩ መደሰታቸውን ጠቁመው፣ ከዚህ በፊት በአገልግሎት ምክንያት የሚደርስባቸውን እንግልት በመቀነስ በመንግሥት አገልግሎት ላይ ያለውን ቅቡልነት እና ተዓማኒነት ያሳድጋል ብለዋል።
በማዕከሉ 9 ተቋማት የሚገኙ ሲሆን፣ 31 አገልግሎቶችን በአንድ ጊዜ አጣምሮ እንደሚሰጥም ተመላክቷል።
በተመስገን ተስፋዬ