Search

የመደመር ትውልድ የቀይ ባሕር ጎረቤት ሳይሆን ባለቤት ነው!

ማክሰኞ ሰኔ 02, 2018 44

የአንዲት ሀገር ጂኦ-ፖለቲካዊ ከፍታም ሆነ ዝቅታ የሚወሰነው በትውልዶች የሃሳብ ቅብብሎሽ እና በሚይዙት ፖለቲካዊ እሳቤ ልክ ነው።

የኢትዮጵያ የውኃ በር መዘጋት እና ከተፈጥሯዊ የቀይ ባሕር ዳርቻዎቿ መገፋት የተፈጠረው በአጋጣሚ ወይም በአንድ ጀምበር የተከሰተ ዕዳ አይደለም።

ይልቁንም፣ ላለፉት አሥርታት በተከታታይ የተፈራረቁ የፖለቲካ ልሂቃን እና ትውልዶች በፈጸሙት ስትራቴጂካዊ እና ፖለቲካዊ ስህተት የተወለደ ታሪካዊ ግድፈት ነው።

ዛሬ ላይ ግን፣ ይህንን የታሪክ ስብራት ለመጠገን፣ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ዳግም ያለማወላወል ለማስጠበቅ እና የታጠፈውን ብሔራዊ ክብር ከፍ ለማድረግ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ተከፍቷል።

ይህን ታሪካዊ እና ትውልዳዊ ኃላፊነት ለመሸከም የሚያስችል ብቃት፣ ዝግጅት እና የጠለቀ ዕውቀት ያለው "የመደመር ትውልድ" ተነስቷል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (/) በተጻፈው «የመደመር ትውልድ» መጽሐፍ ላይ በግልጽ እንደተተነተነው፣ የትውልዶች የሃሳብ መዛነፍ ሀገርን በማፍረስም ሆነ ሉዓላዊነትን አሳልፎ በመስጠት ረገድ የነበረው ሚና እጅግ ከፍተኛ ነው።

መጽሐፉ ቀደምት ትውልዶችን በጥልቀት ሲቃኝ፣ አንደኛው ነባሩን እሴት ብቻ አጥብቆ የሚይዝና የዘመኑን አዳዲስ የዕውቀት ፍሰቶች ለመቀበል የተቸገረ አጥባቂ ነበር ይለዋል።

ተከታዩ ትውልድ ደግሞ ከውጭ በመጡ ርዕዮተ ዓለሞች ተገፋፍቶ፣ የሀገሩን ነባር እሴት፣ ታሪክ እና ተቋማት ከመሰረቱ ንዶ አዲስ ሥርዓት ለመገንባት የሞከረ አብዮታዊ ወይም አፍራሽ ትውልድ ሆኖ አልፏል።

እነዚህ የትውልድ ጽንፎች ሀገራችንን ከባድ ዋጋ አስከፍለዋታል። በጽንፈኝነት፣ በመጠፋፋት እና በዜሮ ድምር ፖለቲካዊ እሳቤዎች ኢትዮጵያ ውስጣዊ አቅሟ ሲዳከም፣ የውጭ ጫናዎችን የመቋቋም አቅሟ ክፉኛ ተሸረሸረ።

በዚህም ምክንያት፣ በዓለም አቀፍ መድረክ ተሰሚነቷ አሽቆልቁሎ ጂኦ-ፖለቲካዊ አቅሟ ሲሽመደመድ፣ በመጨረሻም ታሪካዊ የውኃ በሮቿን አጥታ የየብስ እስረኛ ለመሆን ተገደደች።

የመደመር ትውልድ ግን ከእነዚህ የታሪክ ጽንፎች የጸዳ፣ ሚዛናዊ እና አርቆ አሳቢ ትውልድ ነው።

ይህ አዲስ ትውልድ ያለፈውን ዘመን ጠባሳ እያከከ እና ታሪክን እየወቀሰ የሚኖር ሳይሆን፣ ካለፈው ስህተት ተምሮ የነገውን ብሩህ ተስፋ የሚገነባ ነው።

በመጽሐፉ አገላለጽ መሠረት፣ የመደመር ትውልድ አፍራሽም፣ ነባሩን አጥባቂም አይደለም።

ይልቁንም፣ ጠጋኝ፣ አቃፊ እና አዳዲስ ሳይንሳዊ እሳቤዎችን ከነባር አወንታዊ እሴቶች ጋር አዋህዶ ሀገራዊ አቅም መፍጠር የሚችል ነው።

ይህ ትውልድ የኢትዮጵያን ቀይ ባሕር የማስመለስ እና የባሕር በር ባለቤት የመሆን ጥያቄ በአዲስ እና በሰለጠነ መንገድ ያነሳል።

ከቀደመው አፍራሽ የፖለቲካ ባህል በመውጣት፣ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በጋራ የማደግ ስትራቴጂን በመንደፍ፣ የባሕር በር ጥያቄን ሳይንሳዊ፣ ሕጋዊ እና ዲፕሎማሲያዊ በሆነ መንገድ እያቀረበ ይገኛል።

የመደመር ትውልድ የኢትዮጵያን የሕዝብ ብዛት፣ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እና የቀጣናውን ተለዋዋጭ ጂኦ-ፖለቲካ በጥልቀት የመተንተን አቅም ስላለው፣ የባሕር በር ማግኘት ለሀገራችን የህልውና እና የብሔራዊ ደህንነት ጉዳይ መሆኑን ለዓለም ማህበረሰብ በማስረጃ አስደግፎ ማስረዳት ችሏል።

ከዚህም ባሻገር፣ ይህ ትውልድ ታላላቅ ሀገራዊ ግቦችን ማሳካት የሚቻለው በጠንካራ የውስጥ አንድነት መሆኑን ጠንቅቆ ያውቃል።

ስለሆነም ሕብረብሔራዊነትን እንደ ሀገራዊ ውበት እና የጥንካሬ ምንጭ አድርጎ ይወስደዋል።

የሁሉንም ማንነቶች፣ ቋንቋዎች እና ባህሎች በወንድማማችነት ማዕቀፍ ውስጥ በማስተናገድ፣ ጠንካራ እና ያልተሰነጣጠቀች ኢትዮጵያን መገንባት ዋና ዓላማው ነው።

ይህ የውስጥ አንድነት እና ሕብረብሔራዊ መግባባት፣ ትውልዱ የውጭ ጫናዎችን እንዲቋቋም እና የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ያለማወላወል እንዲያስጠብቅ ብርቱ የጀርባ አጥንት ይሆነዋል።

የመደመር ትውልድ የኢትዮጵያን የትናንት ስብራቶች ጠግኖ፣ የዛሬን ፈተናዎች በብልሃት ተሻግሮ፣ የነገዋን ገናና ኢትዮጵያ የሚገነባ ብሩህ እና ቆራጥ ትውልድ ነው።

ስሜታዊነትን በዕውቀት፣ ጉልበትን በረቀቀ ዲፕሎማሲ፣ መከፋፈልን በኅብረ ብሔራዊ አንድነት የተካው ይህ ትውልድ፣ የሀገሩን ብሔራዊ ክብር አሳልፎ አይሰጥም።

በመደመር ፍልስፍና የታነጸው እና በበቂ ዕውቀት የተደራጀው ይኸው ትውልድ፣ ኢትዮጵያን ከራቀችበት የቀይ ባሕር ዳርቻዎች እንደሚመልሳት እና ታሪካዊ ክብሯን በተግባር እንደሚያረጋግጥ አያጠራጥርም!

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ