Search

የጉባ ብሥራት ጅማሮ፡ ሜጋ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ የሚያፋጥኑበት አዲሱ ምዕራፍ

ማክሰኞ ሰኔ 02, 2018 57

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ማዕቀፍ ያስተላለፉት ታሪካዊ መልዕክት እና ያወጇቸው ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ጅማሮ ብሥራት ዛሬ በላብ እና በጥናት ወደ ተጨባጭ ተግባር እየተቀየሩ ይገኛሉ።

በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በልዩ ትኩረት ከጠቀሷቸውና የጉባ ብሥራት ተብለው ከሚጠሩት ሜጋ ፕሮጀክቶች መካከል ግዙፉ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት፣ የማዳበሪያ ፋብሪካ እና የተፈጥሮ ጋዝ ማቀነባበሪያ ፕሮጀክቶች ዛሬ በተግባራዊ የሥራ ምዕራፍ ላይ ይገኛሉ።

በመሠረተ ልማት ዘርፍ ኢትዮጵያን የአፍሪካ አዲሱ የአቪዬሽን እና የንግድ ማዕከል ለማድረግ የታለመው ግዙፉ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት በመንግሥት ሙሉ ትኩረት ግንባታው ተጀምሯል።

ይህ ታላቅ ፕሮጀክት ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ በዓመት 100 ሚሊዮን በላይ መንገደኞችን የማስተናገድ ግዙፍ አቅም የሚኖረው ሲሆን፣ የሀገራችንን የቱሪዝም ዘርፍም ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግረዋል።

በተመሳሳይ የኢትዮጵያን የግብርና ምርታማነት በዘላቂነት ለመደገፍና በምግብ ዋስትና ራስን ለመቻል ታልሞ የተጀመረው የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታም በተቀናጀ ሁኔታ እየተከናወነ ይገኛል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሶማሌ ክልል ጎዴ በመገኘት የዚህን ስትራቴጂካዊ ፕሮጀክት የክንውን ሂደት መጎብኝታቸው ለመርሃ ግብሩ የተሰጠውን ከፍተኛ ሀገራዊ ትኩረት ያሳያል።

የተፈጥሮ ጋዝ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ የመጀመሪያው ምዕራፍ በይፋ ተመርቆ ሥራ የጀመረ ሲሆን፣ የዚሁ ፕሮጀክት ግዙፍ ማስፋፊያ አካል የሆነው ቀጣይ ሥራም በስኬት ተጀምሯል፡፡

ይህ ሜጋ ፕሮጀክት ኢትዮጵያ በኢነርጂ እና በኢንዱስትሪ ዘርፍ ወደ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ መሸጋገሯን የሚያሳይ ታሪካዊ እመርታ ነው።

ፕሮጀክቱ ሀገራችን ለዘመናት ለነዳጅ እና ማዳበሪያ ምርቶች ስታወጣ የነበረውን በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር የውጭ ምንዛሬ በከፍተኛ ደረጃ በመቀነስ፣ ወደ ዘላቂ እና ለአካባቢ ተስማሚ የኃይል አማራጮች እንድትሸጋገር ያደርጋታል።

የዚህ ታላቅ የሽግግር ውጤት ደግሞ አሁን ዓለም በመካከለኛው ምሥራቅ ባለው ጂኦፖለቲካዊ ግጭት እና ቀውስ ምክንያት የነዳጅ ዋጋ መዋዠቅ በገጠማት በአሁኑ ወቅት በትራንስፖርት ዘርፋችን ላይ ትልቅ ማክሮ-ኢኮኖሚያዊ እፎይታን እየፈጠረ ይገኛል።

ከተለምዷዊ የነዳጅ ፍጆታ ወጥተው በአረንጓዴ ኢነርጂ እና በሀገር ውስጥ በሚመረት የተፈጥሮ ጋዝ የሚሠሩ የሕዝብ ማመላለሻ እና የጭነት ተሽከርካሪዎች ወደ ገበያ በስፋት መግባታቸው የኢትዮጵያ የኢነርጂ ፖሊሲ በተግባር እየተቀየረ ለመሆኑ ቁልፍ ማሳያ ነው።

ከታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማጠናቀቂያ ምዕራፎች ጀምሮ የተነሱት ታላላቅ ሀገራዊ ራዕዮች በቃል ደረጃ ብቻ የቀሩ ሳይሆኑ በተጨባጭ የልማት ውጤቶች መሬት ላይ እየተገለጡ መሆናቸውን ተረጋግጧል።

በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ከኃይል ማመንጨት ባለፈ የኢነርጂ ሽግግርን፣ የኢንዱስትሪ ዕድገትን፣ የግብርና ራስን መቻልን እና የመሠረተ ልማት አብዮትን በአንድ ላይ እውን የምታደርግበትን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ በቁርጠኝነት እየጻፈች ትገኛለች።

በሃና ምንዳሁን