ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በታሪካዊቷ የወልድያ ከተማ የተገነቡ የተለያዩ ዐበይት የልማት ፕሮጀክቶችን መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የኢትዮጵያ ጉዞ ወደፊት መሆኑን እና የትኛውም የጠላት ዕቅድ ሀገራችንን ከጀመረችው የልማት ጉዞ ሊያስቆማት እንደማይችል አረጋግጠዋል።
ወልድያን የየጁዎች ሥልጣኔ መገኛ፣ እንዲሁም "የልማት፣ የፅናት እና የድል አምባ" ሲሉ የገለጿት ሲሆን፣ አመራሩ እና ሕዝቡ በአንድነት ተግተው ያሳኳቸውን ፕሮጀክቶች መርቀዋል።
እነዚህ ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያ ወደፊት ለመገስገሷ ማረጋገጫዎች መሆናቸውን ጠቅሰው፣ በዋናነት ከተማዋን የማዘመን እና የኮሪደር ልማትን የማስፋፋት ሥራዎች፣ ዘመናዊ የሕዝብ እና የዲጂታል ቤተ-መጻሕፍት ግንባታ እንዲሁም የንግድ እና የኢንዱስትሪ ማዕከላትን ያካተቱ እንደሆኑ ገልጸዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጽ ባሰፈሩት መልዕክታቸው፣ የኢትዮጵያ መንገድ ‘መደመር' ግቧም 'ብልጽግና' መሆኑን አጽንዖት ሰጥተዋል።
አያይዘውም ትግላቸው መንገዳቸውን ክፍፍል፣ ግባቸውን ደግሞ ድህነት ካደረጉ "ቆሞ-ቀሮች" ጋር መሆኑን ጠቁመው፣ “የኢትዮጵያን ልዕልና ሳናረጋግጥ አንቆምም” ብለዋል።
"ጠላት የፈለገውን ያህል ቢያቅድ ከጉዟችን አያስቆመንም፤ ወልድያ ለዚህ ምስክር ናት" ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሺህ ጠላት ቢሰበሰብ የኢትዮጵያን ጉዞ ለአፍታም ሊያስቆመው እንደማይችል በጽኑ አቋም ገልጸዋል።