Search

የሐሳብ ገበያችን መዳኛ፦ ከሐሰት እና ከስሜት አዙሪት ወደ እውነት እና ዕውቀት!

ማክሰኞ ሰኔ 02, 2018 48

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) አራተኛ የመደመር መጽሐፍ በሆነው "የመደመር መንግሥት" ገጽ 390 ላይ "ለሐሳብ ገበያ መሞቻው ሐሰትና ስሜት ሲሆን፣ መዳኛው እውነት እና ዕውቀት ነው" የሚል ድንቅ ሐሳብ ሰፍሯል።

ይህ ፍልስፍናዊ እሳቤ የዛሬዋን ኢትዮጵያ የፖለቲካ አካሄድ እና ማኅበራዊ መስተጋብር ለመቃኘት እጅግ ቁልፍ መነሻ ነው።

አገላለጹ ሀገራችን ያለችበትን የሐሳብ ልውውጥ ምኅዳር የሚጠቁም ብቻ ሳይሆን፣ ወደፊት ለምትገነባው የተረጋጋችና የበለጸገች ሀገር መውጫ መንገዱን ያመላክታል።

ባለፉት ዓመታት በሀገራችን የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋት የተደረገው ጥረትና የዲጂታል ሚዲያ መስፋፋት በርካታ መልካም አጋጣሚዎችን ይዞ መጥቷል።

ይህ መልካም አጋጣሚ ቢኖርም፣ የሐሳብ ገበያው ግን በአሳሳች መረጃዎች፣ በተደራጁ የሐሰት ዘመቻዎች እና በስሜታዊነት አዙሪት ውስጥ እንዲወድቅ ተደርጓል።

ሐሰት እና ስሜት የሰፈኑበት የሐሳብ ገበያ ደግሞ ቀስ በቀስ ወደ ጽንፈኝነት፣ ወደ ጥላቻ ትርክቶች እና ወደ "እኛ እና እነሱ" የጎራ ክፍፍል ያመራል።

በዚህ ዓይነቱ መርዛማ ድባብ ውስጥ እውነተኛ መረጃዎች እና በዕውቀት ላይ የተመሠረቱ የፖሊሲ አማራጮች ቦታ ያጣሉ።

ሰዎች ነገሮችን በሚዛናዊነት ከማየት ይልቅ በስሜት እንዲነዱ ሲደረግ ሀገራዊ የሆኑ የልማት እና የሰላም ጥያቄዎች ጭምር የራሳቸውን መዋቅራዊ ይዘት አጥተው ለፖለቲካ መጠቀሚያነት ይዳረጋሉ።

ይህም የኅብረተሰቡን የእርስ በርስ መተማመን በእጅጉ በመሸርሸር እና ሐሳቦችን ከማንነቶች ጋር በማያያዝ ሰፊ "የእምነት ቅናሽ" ይፈጥራል፤ የሐሳብ ገበያውንም ሙሉ በሙሉ ይገድለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) ይህን የዘመናት የስሜታዊነት እና የሐሰት አዙሪት ለመስበር የመደመር እሳቤን መዋቅራዊ እና ተቋማዊ መሠረት በማስያዝ ላይ ይገኛሉ።

መደመር ጥላቻን እና ስሜታዊነትን ወደ ጎን በመተው ፖለቲካን ወደ እውነተኛ የሐሳብ ገበያነት ለመቀየር የሚጥር ሀገር በቀል ፍልስፍና ነው።

በዚህ መሠረት መንግሥት የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ ዘርፎችን በማዘመን ረገድ ፈጠራን፣ ፍጥነትንና "ዝላይ ስትራቴጂዎችን" እየተጠቀመ ይገኛል።

ይህ ለውጥ የማወቅ ጉጉት ያለው፣ ለውይይት ባህል ቅርብ የሆነ፣ ዐርበኛ እና የሰውን ልጅ ክብር የሚያስጠብቅ "የመደመር ትውልድ" ለመገንባት የሚያስችል ሥርዓተ ትምህርታዊ እና ሥነ ልቦናዊ ዝግጅትን ያካትታል።

መደመር ትውልዱን በሐሳብ ገበያው ውስጥ ያለ አቅጣጫ እንዲንከራተት አይተወውም።

ይልቁንስ "እውነቱ ይህ ነው፣ ማሰብ የሚገባችሁ በዚህ መንገድ ነው፤ ሆኖም ግን ስህተት ካገኛችሁበት የመተቸት መብታችሁ የተጠበቀ ነው" የሚለውን ሚዛናዊ አቀራረብ ተግባራዊ ያደርጋል።

በዚህም ወጣቱ ከዲጂታል ዓለም መዛባት ተጠብቆ እውነትን እና ዕውቀትን እንዲጨብጥ እየተደረገ ነው።

የኢትዮጵያ ዘላቂ መዳኛ እውነት እና ዕውቀት ብቻ መሆናቸውን በሚገባ መረዳት ያስፈልጋል።

ሀገራዊ አንድነት እና ብልጽግናን ማረጋገጥ የሚቻለው በጊዜያዊ ስሜት እና በፕሮፓጋንዳ ሳይሆን፣ በጠንካራ የዕውቀት መሠረት እና በሐቀኛ ውይይት ብቻ ነው።

ለዚህ ደግሞ የተናጠል ባህል እና ቋንቋን ሳናጠፋ እንደ ሀገር አብሮነታችንን ሊያጠናክር የሚችል የጋራ ብሔራዊ ትርክት መገንባት ይኖርብናል።

የውይይት እና የስምምነት እሴት ያላቸውን ሀገር በቀል ዕውቀቶቻችንን በመጠቀም የሐሳብ ገበያውን ማዳበር ይቻላል።

የሽምግልና ሥርዓትን የመሰሉ ትውፊታዊ የዕርቅ እና የውይይት ጥበቦችን ከመደበኛው የሐሳብ ምኅዳር ጋር በማዋሃድ የሰላም እና የልማት ውይይቶቻችንን መሠረት ማጠናከር እንችላለን።

ለኢትዮጵያ የፖሊሲ ቀውሶች፣ የኢኮኖሚ ተግዳሮቶች እና ማኅበራዊ ስብራቶች መፍትሔው በሐሳብ ገበያው ውስጥ የሚደረግ የዕውቀት መሻት እና ለእውነት መገዛት ብቻ ነው።

እውነት እና ዕውቀት ባልነገሡበት ሀገር ውስጥ የሚነሳ ማንኛውም የሐሳብ ማዕበል አፍራሽነቱ ከፍ ያለ ነው።

ሀገርን በጽኑ መሠረት ላይ ለማቆም ሁሉም ወገን አሳሳች መረጃዎችን እና ስሜት ነክ ጥላቻዎችን በዕውቀት አጥር መከላከል፣ የሐሳብ ገበያውን የእውነት እና የዕውቀት ማደሪያ ማድረግ ይገባዋል።

ይህን የሐሳብ ገበያ መታደግ የመንግሥት ወይም የጥቂት ምሁራን ኃላፊነት ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም መጻኢው የኢትዮጵያ እጣ ፈንታ የሚያሳስበው የእያንዳንዱ ሀገር ወዳድ እና ዜጋ የቤት ሥራ ጭምር ነው።

በለሚ ታደሰ