የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት በመቆም ታሪክ የማይረሳውን እና በመላው ዓለም ፊት ሀገሩን ከፍ ያደረገውን 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ በታላቅ ስኬት አጠናቅቋል።
ይህ ምርጫ ዜጎች የሚመሯቸውን መሪዎች በነፃነት የመረጡበት መድረክ ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያን መፍረስ እና መበታተን ይመኙ ለነበሩ ታሪካዊ ጠላቶች ዳግም የማያገግሙበትን ታላቅ የፖለቲካ ሽንፈት ያከናነበ የዴሞክራሲ ከፍታ ነው።
ይህ ምርጫ ስኬታማ የተባለበት ዋነኛው ምክንያት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የተለያዩ የሀሰት ፕሮፓጋንዳዎችን እና የሽብር ዛቻዎችን ሙሉ በሙሉ ውድቅ በማድረግ በነቂስ ወጥቶ ድምፁን በመስጠቱ ነው።
ከዚህም በተጨማሪ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያሳየው ገለልተኛ ተቋማዊ አቅም፣ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰላማዊ ተሳትፎ እንዲሁም የጸጥታ አካላት ሕዝቡ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ ያደረጉት ከፍተኛ ጥረት ለምርጫው ስኬት ትልቅ ድርሻ አበርክተዋል።
ምርጫው አይሳካም ሲሉ የነበሩ የውጭ እና የውስጥ ኃይሎች፣ ሕዝቡ በሰላማዊ እና በሰለጠነ መንገድ ረጃጅም ሰልፎችን ይዞ ሲመርጥ በማየታቸው ሀሳባቸው መክኖባቸዋል።
ሕዝቡ በተግባር ያሳየው ይህ የፖለቲካ ብስለት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና የዴሞክራሲ ጉዞ ማንም ሊገታው እንደማይችል ለዓለም ያስመሰከረ ታላቅ ብሔራዊ ድል ሆኗል።
በዚህ ምርጫ ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው ስኬት በራስ አቅም ሀገራዊ ተቋማትን ማጠናከር መቻሏን አጉልቶ አሳይቷል።
በገንዘብ እና በቴክኖሎጂ እገዛ ስም የምርጫውን ሂደት ለማነቅ የሞከሩ አካላትን በማሳፈር፣ ምርጫው ፍጹም ሰላማዊ፣ ነፃ፣ ግልጽ እና ተዓማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ተደርጓል።
ይህም ኢትዮጵያ ከማንም ጥገኝነት ወጥታ የራሷን ዕድል በራሷ የመወሰን ሙሉ ብቃት እንዳላት ያሳየ ነው።
ውድቀቷን ይመኙ ለነበሩ አካላት ደግሞ ትልቅ የሥነ ልቦና እና የፖለቲካ ስብራት ሆኖባቸዋል።
በምርጫው ኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታዋን ስታጠናክር፣ የሀገርን ሰላም የማይሹ ኃይሎች ግን ሙሉ በሙሉ በሕዝቡ ውሳኔ የተሸነፉበት እና የተጋለጡበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
በጥቅሉ ምርጫው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሀገሩ ያለውን ጽኑ ፍቅር እና ለአንድነቱ ዘብ የቆመ መሆኑን በድጋሚ ያረጋገጠበት ታሪካዊ ድል ነው።
በሃና ምንዳሁን