Search

በልዩ የምርጫ ጣቢያዎች የተካሄደው የድምፅ አሰጣጥ ሂደት በአብዛኛው ተጠናቅቋል - ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

ማክሰኞ ሰኔ 02, 2018 49

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፣ ማለዳ 12 ሰዓት ላይ በልዩ የምርጫ ጣቢያዎች የተጀመረው የድምፅ መስጠት ሂደት በአብዛኛዎቹ ጣቢያዎች በስኬት መጠናቀቁን ገልጸዋል።

ቦርዱ በቂ መረጃዎችን ሰብስቦ፣ ለምርጫ አስፈፃሚዎች አስፈላጊውን ሥልጠና በመስጠት እና የሎጀስቲክስ እና ሰነዶች ሥርጭትን በብቃት በማከናወን ዛሬ በልዩ የምርጫ ጣቢያዎች ድምፅ የመስጠት ሂደቱ ያለምንም እንከን እንዲካሄድ አድርጓል።

በዚህም መሠረት በወታደራዊ ካምፖች እና በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ካምፖች ውስጥ፣ በሚገኙ 85 በላይ ልዩ ጣቢያዎች ምርጫው በሰላም ተካሂዷል።

በድምፅ አሰጣጥ ሂደቱም ልዩ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው መራጮች እንደማንኛውም ዜጋ ተገቢው እገዛ መደረጉን ሰብሳቢዋ አስረድተዋል።

በቅድመ ምርጫው ሂደት የመራጮች ምዝገባ እና የትምህርት አሰጣጥ ላይ 6 ሺህ 600 የሚሆኑ አስተባባሪዎች እንዲሁም 1 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኛ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ቁልፍ ሚና መጫወታቸውን ሰብሳቢዋ አስታውቀዋል።

ለዚህም ስኬት ቦርዱ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ማድረጉን ጠቁመዋል።

ቀደም ሲል በተካሄደው አጠቃላይ ምርጫ፣ የድምፅ ቆጠራው ተጠናቅቆ በሁሉም የምርጫ ክልሎች ውጤት በይፋ የተለጠፈ መሆኑን ሰብሳቢዋ አረጋግጠዋል።

እስካሁንም 816 የምርጫ ክልሎች ውጤቶች ወደ ማዕከል የደረሱ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ቀሪዎቹ በመጓጓዝ ላይ እንደሚገኙ በመግለጫቸው አብራርተዋል።

በለሚ ታደሰ