በኢትዮጵያ በየዓመቱ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ወጥቶበት ከውጭ ይገባ የነበረውን ከአንድ ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ ስንዴ በሀገር ውስጥ ምርት መተካት ችላለች።
ሀገራችን ለዘመናት የዘለቀውን የምግብ እርዳታ ጥገኝነት በመስበር፣ በዘመናዊ ግብርና ራስን በመመገብ ስትራቴጂ የምግብ ሉዓላዊነቷን እያረጋገጠች ትገኛለች።
ኢትዮጵያ አሁን "ምጽዋት ይብቃኝ" በሚል ጽኑ አቋም የውጭ ጣልቃ ገብነትን እና የእጅ መጠምዘዝን የሚከላከል የግብርና አብዮት እያካሄደች ነው።
በግብርና ሚኒስቴር የሚኒስትሩ አማካሪ ጌታቸው ድሪባ (ዶ/ር) ከኢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፣ ይህ ውጤት ሀገራችን የውጭ ምንዛሬ አውጥታ ስንዴ ስትገዛ የነበረበትን ታሪክ የቀየረ ትልቅ ስኬት ነው።
ለዚህ አመርቂ ውጤት መመዝገብ ዋነኛ ምክንያት የሆኑት አዳዲስ የግብርና አሠራሮች መሆናቸውን የጠቀሱት አማካሪው፣ በተለይም የኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣቱን አክለዋል።
በአሁኑ ወቅትም በኢትዮጵያ ከ20 እስከ 25 በመቶ የሚሆነው የእርሻ ሥራ በትራክተር እና በዘመናዊ ማሽነሪዎች እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በግብርናው ዘርፍ እየተመዘገበ ያለው ይህ ሥር ነቀል ለውጥ ለኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነት የማይናወጥ መሠረት ከመፍጠሩም ባሻገር፣ የሀገራችንን ውስጣዊ አቅም በማጎልበት በቀጣይ ለቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስር እና አቅርቦት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ዶ/ር ጌታቸው አብራርተዋል።
በቢታኒያ ሲሳይ