ከስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ማግስት አንስቶ ወደ ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ዋዜማ ስንሸጋገር፣ የኢትዮጵያ ከተሞች የፃፉት ታሪክ የግንባታና የፕሮጀክት ብቻ ሳይሆን የሰዎችም ጭምር ነው።
በመደመር ዕይታ፣ ከተሜነትና ልማት ሰውን ከዘነጋ፣ እንዲሁም የሰውን ልጅ ክብርና ደህንነት ካላረጋገጠ ባዶ ኮንክሪት ከመሆን አይዘልም። ጫፍ የወጣ የካፒታሊዝም ሥርዓት ድሃውን ሲዘነጋና ሲጥል፣ የመደመር ፍልስፍና ግን "ሰውን ማዕከል ያደረገ" ልማትን አጥብቆ ይከተላል።

በዚህም ባለፉት አምስት ዓመታት ከተሞቻችን አካታችና ለሁሉም ዜጋ በተለይም ለአቅመ ደካሞች አስታዋሽና ባለውለታ እንዲሆኑ ከፍተኛ ርብርብ ተደርጓል።
የመደመር ትውልድ "ልማት ሰውን ዘንግቶ ሊሳካ አይችልም" በሚል መርህ ያከናወናቸው አበይት ሰው ተኮር ስራዎች የሚከተሉት ናቸው፡-
የተማሪዎች ምገባና የማዕድ ማጋራት “ነገን የምንገነባው ዛሬ ህፃናትን በመመገብ ነው” በሚል እሳቤ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተማሪዎችን ተጠቃሚ ያደረገው የምገባ ፕሮግራም በከተሞች በስፋት ተተግብሯል።

ይህም የድሃ ቤተሰብ ልጆች በባዶ ሆዳቸው እንዳይውሉ ከማድረጉም በላይ፣ ጥንታዊውን ኢትዮጵያዊ የመረዳዳት ባህል በማዘመን “የማዕድ ማጋራት” መርሃ-ግብር የበርካታ ተጋላጭ ዜጎችን ህይወት የታደገ ዘላቂ ባህል ሆኗል።
የእሁድ ገበያና የሌማት ትሩፋት የኑሮ ውድነት የከተማ ነዋሪውን ጫንቃ በፈተነበት ወቅት፣ የግብይት ሰንሰለትን በማሳጠር አምራቹንና ሸማቹን በቀጥታ የሚያገናኙ 2,127 የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች በመላው ሀገሪቱ ተስፋፍተው ነዋሪው የፍጆታ እቃዎችን በቅናሽ ዋጋ እንዲያገኝ አድርገዋል።
ከዚህም ጎን ለጎን ዜጎች በ“ሌማት ትሩፋት” እና በከተማ ግብርና በጓሯቸው አምርተው በምግብ ራሳቸውን እንዲችሉና የኢኮኖሚ አቅማቸውን እንዲገነቡ አስችሏል።
የቤት እድሳትና የህፃናት ፕሮግራም ከተሜነት የሰውን ልጅ ክብር መመለስ አለበት በሚለው ጥልቅ የመደመር እሳቤ፣ ለዘመናት በፈራረሱና ለጤና አደገኛ በሆኑ ሰፈሮች ውስጥ ይኖሩ የነበሩ አቅመ ደካማ ዜጎችን ህይወት ለመቀየር ሰፊ ዘመቻ ተካሂዷል።
በበጎ ፈቃደኞችና በመንግስት ቅንጅት በሺዎች የሚቆጠሩ የአቅም ደካማ ቤቶች ታድሰዋል፤ እንዲሁም 166,207 አዳዲስ ደረጃቸውን የጠበቁ ቤቶች ተገንብተው ለዜጎች ተላልፈዋል። ለነገው ትውልድ ከተሰጠው ልዩ ትኩረት አኳያም በፌዴራልና በክልል ደረጃ 217 የህፃናት ማቆያዎች ተቋቁመዋል።
የተረሱ ጀግኖችንና የሃገር ባለውለታዎችን የሚያስታውስ ሰው ተኮርነት፣ የመደመር ትውልድ ልዩ ባህርይው ዛሬን ብቻ የሚኖር የራሱን ዘመን ብቻ የሚያወድስ ሳይሆን ትናንትን ለዛሬ ያቆየ ጀግኖችንም በአግባቡ እውቅና በመስጠት እና ድጋፍና እንክካቤ በማድረግ ዛሬንና ነገን ማስተሳሰርም መለያው ነው። በዚህም አዲስ አበባ በብዙ ዘርፎች ሃገራቸውን ያገለገሉ ጀግኖችን አስታውሳለች ፣ደርሳላቸው ደጋፊና አስታዋሽ ሆናለች።
በጥቅሉ ከስድስተኛው እስከ ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ዋዜማ የተጓዝንባቸው የ5ቱ ዓመታት ገፆች፣ የቃላት ሳይሆን የላብና የተግባር ድርሳናት ናቸው። የመደመር ትውልድ አሮጌውን፣ አፍራሽና የቸልተኝነት የፖለቲካ ባህል ቀብሮ፣ ከተሞቻችንን የውበት፣ የርኅራኄና የብልፅግና ተምሳሌት አድርጓቸዋል።
ይህ ሰውን ማዕከል ያደረገው የልማት ጅረት፣ ለቀጣዩ ትውልድ የምትመችና ክብሯ የተጠበቀ የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚያስችል ጽኑ መሠረት የጣልንበት ታሪካዊ ምዕራፍ ነው።