ረቂቅ አዋጁ አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶና አርብቶ አደሮች የግብርና ቢዝነስ ኩባንያ በጋራ እንዲያደራጁ እንዲሁም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እንዲደገፉ የሚያስችል መሆኑ ቋሚ ኮሚቴው ገልጿል።
ይህ የተገለጸው፤ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከግብርና ሚኒስቴር እንዲሁም ከኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ጋር የአስረጅዎች ውይይት መድረክ ባካሄደበት ወቅት ነው።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ሰለሞን ላሌ እንደገለጹፁት፣ የረቂቅ አዋጁ አነስተኛ ይዞታ ያላቸውን አርሶ አደሮች፣ አርብቶ አደሮች እና ከፊል አርብቶ አደሮችን በግብርና ቢዝነስ ኩባንያ በጋራ በማደራጀት የፋብሪካ ባለቤት እንዲሆኑ፣ ወደ መካከለኛ አልሚነት እንዲሸጋገሩ፣ ምርታማነትን እንዲያሳድጉ፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና በዘርፉ ለዜጎች የስራ እድል በመፍጠር ህብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን በማስቻል ረገድ ጉልህ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
አርሶ አደሮች መሬታቸውን፣ እንስሳቶቻቸውን እና ጉልበታቸውን ወደ ካፒታል በመለወጥ ከደላላ ተጽዕኖ ነፃ በመሆን ተጠቃሚ እንዲሆኑ ረቂቅ አዋጁ የሚረዳ መሆኑን ሰብሳቢው አያይዘው አመላክተዋል።
ረቂቅ አዋጁ ሀገሪቱ ለተያዘችው ቀጣይ የዕድገት አቅጣጫ የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን፣ ግብርናን ከተለምዷዊ ሥርዓት ወደ ዘመናዊና ትርፋማ የንግድ ሥርዓት ለመቀየር፣ የሀገር ውስጥ ገቢ እና የውጭ ምንዛሬ ለማሳደግ፣ የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
በረቂቅ አዋጁ ላይ “አነስተኛ ይዞታ” ለሚለው ቃል የተሰጠው ትርጓሜ የክልሎችን የመሬት አወቃቀር ሥርዓት ያላገናዘበ በመሆኑ፣ የክልሎችን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ ሊሻሻል እንደሚገባ የተከበሩ አቶ ሰለሞን ላሌ አሳስበው፤ በተጨማሪም የሴቶች ተሳትፎን በሚመለከት፣ በስራ አመራር ቦርድ ውስጥ የሚሳተፉ ሴቶችን ቁጥር ከመወሰን ይልቅ በመቶኛ ወይም ፍትሃዊ ውክልናን በሚያሳይ መልኩ መቀመጥ እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶ/ር )በበኩላቸው፣ ቋሚ ኮሚቴው ፣ ከቦርድ እንዲሁም በስራ አስኪያጅ አወቃቀር እና አደረጃጀት ላይ የተቀመጡ ኃላፊነቶችንና ተግባራት በተመለከተ ያነሳቸውን ሀሳቦች እና ጥያቄዎች በመቀበል ቀጣይ ማስተካከያ እንደሚደረግ ገልጸዋል።

የግብር ሚኒስቴር የህግ ስራ አስፈጻሚ አቶ በለጠ ሰይፉ በበኩላቸው፣ ረቂቅ አዋጁ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ በሚገኙ አርሶና አርብቶ አደሮች ህይወት ላይ ዘላቂነት ለውጥ ለማምጣት እንዲሁም የገጠር እና የግብርና ትራንስፎርሜሽንን ለማረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
ረቂቅ አዋጁ የዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን ታሳቢ ያደረገ በመሆኑ በዘርፉ ለሀገር ዕድገት መሰረት የሚጥል መሆኑን ሥራ አስፈፃሚው አያይዘው አስረድተዋል።