Search

ከታሰበው ጊዜ ቀድሞ የተሳካው የ"5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደሮች" መርሐ ግብር እና አዲሱ ግብ

ሓሙስ ሰኔ 04, 2018 87

ኢትዮጵያ የአዲሱ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲዋ ምሰሶ አድርጋ ከያዘቻቸው ቁልፍ ዘርፎች አንዱ ቴክኖሎጂ ነው።

ኢትዮጵያ አሁን ዓለምን እየቀየረ ባለው የቴክኖሎጂ ዘርፍ ውስጥ ተዋናይ ብቻ ሳትሆን ቀዳሚ ለመሆን በከፍተኛ ትጋት እየሠራች ትገኛለች።

ለዚህም 'ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025' በስኬት በመተግበር አሁን ላይ 'ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030' ስትራቴጂን ወደ ማሳካት ተሸጋግራለች።

በዚህ የዲጂታል ስትራቴጂ ውስጥ ከሚተገበሩት ግዙፍ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ሐምሌ 16 ቀን 2016 . በይፋ የተጀመረው "5 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ኮደሮች" መርሐ ግብር ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) መርሐ ግብሩ በሦስት ዓመት ሊደረስ የታሰበውን ግብ ከሁለት ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ መሳካቱን አስመልክተው የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ከተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች መንግሥት ጋር በመተባበር በዓለም አቀፉ የትምህርት መድረክ ዩዳሲቲ በኩል በሚሰጠው በዚህ ታሪካዊ ፕሮግራም እስካሁን 5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ተመዝግበዋል።

3 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ደግሞ በፕሮግራሚንግ፣ ዳታ ትንተና፣ አንድሮይድ ሶፍትዌር ልማት እና ሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ሥልጠናቸውን በሚገባ አጠናቅቀዋል።

ይህ ስኬት ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂን በተግባር እውን ከማድረግ አንጻር የማይተካ ሚና አለው።

የዲጂታል ስትራቴጂው ሀገራችንን ወደ ዕውቀት መር ኢኮኖሚ ለማሸጋገር እና የቴክኖሎጂ ፈጠራን ለማበረታታት ያለመ ነው።

እነዚህን ዘመናዊ ክህሎቶች የተካኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶችን ማፍራት፣ የሀገራችንን የመረጃ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ እና የዚሁ ሀገራዊ የዲጂታል ሽግግር የጀርባ አጥንት በመሆን ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል።

ይህ የሰው ሀብት ልማት ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እጅግ ግዙፍ ትርጉም አለው።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ዓለም አቀፍ ዕውቅና ባለው የቴክኖሎጂ ክህሎት እና ማረጋገጫ መታጠቃቸው በዓለም አቀፉ የዲጂታል የሥራ ገበያ ላይ በስፋት ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል።

በዚህም ወጣቶች ለራሳቸው ዓለም አቀፍ የሥራ ዕድል ከመፍጠራቸውም ባለፈ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲያስገቡ ሰፊ በር ይከፍታል።

በተጨማሪም አዳዲስ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች እንዲያብቡ በማድረግ የሀገር ውስጥ የፋይናንስ ተቋማት፣ የጤናው ዘርፍ፣ ግብርናው እና የማምረቻ ኢንዱስትሪው በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዘው ምርታማነታቸውን በከፍተኛ ደረጃ እንዲያሳድጉ የኢኮኖሚው ቁልፍ ሞተር ይሆናል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው ይህ ስኬት የጉዞ መነሻ እንጂ ማብቂያ አለመሆኑን በማብራራት፣ እስከ ነሐሴ 2018 . የሠልጣኞችን ቁጥር 7 ሚሊዮን ለማድረስ አዲስ ግብ መታቀዱን አብስረዋል።

በመሆኑም ወጣቶች መጪውን የክረምት ጊዜ በዋዛ ከማሳለፍ ይልቅ፣ ሙሉ በሙሉ በነጻ በሚሰጠው ከዚሁ ሥልጠና ጋር በመቀላቀል የነገ ዓለም አቀፍ የዲጂታል መሪዎች እንዲሆኑ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

በለሚ ታደሰ