የአማራ ክልል መሬት ቢሮ የዜጎችን አንገብጋቢ የቤት መሥሪያ ቦታ ችግር ለመቅረፍ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።

የቢሮው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አወቀ ሲሳይ ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለፁት፤ የክልሉ መንግሥት እየተገበራቸው ካሉ ሰው ተኮር ተግባራት መካከል የዜጎችን የቤት መስሪያ ቦታ አቅርቦት ችግር መፍታት አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህም የመሬት አስተዳደር ሥርዓቱን በማዘመንና በክልሉ ያለውን ጸጋ ለታለመለት ዓላማ ለማዋል ዘርፈ ብዙ ስራዎች ተከናውነዋል።

በዚህም ባለፉት ወራት ውስጥ ለ1 ሺህ 400 በላይ እውቅና ላገኙ የቤት ማኅበራት ከ5 ሺህ 250 ሄክታር በላይ መሬት የተዘጋጀ ሲሆን፣ ለ15 ሺህ 638 ተነሺ ባለይዞታዎችና አርሶ አደሮችም ከ6 ቢሊዮን ብር በላይ ካሳ ተከፍሏል።
ይህ ተግባር የዜጎችን ጥያቄ በመመለስ፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ደረጃ በደረጃ በመፍታትና ሁለንተናዊ ብልፅግናን በማረጋገጥ ረገድ ከባለፉት ዓመታት በተሻለ መንገድ የተከናወነ መሆኑን ኃላፊው ጠቁመዋል።
በተከናወኑት ስራዎችም በደብረ ብርሃን ከተማ፣ በሰሜን ሸዋ፣ ደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ወሎና ምሥራቅ ጎጃም ዞኖች ላይ ያለው አፈፃፀም በመልካም ተሞክሮ የሚወሰድ ሲሆን፣ ባሕር ዳር ከተማን ጨምሮ በሌሎች ከተሞችና ዞኖችም በርካታ ማህበረሰብን ተጠቃሚ ለማድረግ በቂ የመሬት ዝግጅት ተጠናቋል።
በበጀት ዓመቱ መጨረሻም እስካሁን የተሰጣቸውን ጨምሮ በክልሉ ከ68 ሺህ በላይ ዜጎችን የቤት መስሪያ ቦታ ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።
በተጨማሪም ቢሮው መረጃዎችን ሙሉ በሙሉ ዲጂታላይዝድ በማድረግ በክልሉ የሚገኙ 148 ወረዳዎችን ዘመናዊ የገጠር መሬት ካዳስተር ሥርዓት በመገንባት ብሔራዊ የመሬት መረጃ ቋት አዘጋጅቶ ስራ ላይ ማዋል መቻሉን አቶ አወቀ ሲሳይ አስገንዝበዋል።