ከንቲባዋ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የአንድ ከተማ ዓለም አቀፍ መለኪያው ፅዳት፣ ውበትና አረንጓዴነት መሆኑን ጠቅሰው፣ ውብ፣ ፅዱና አረንጓዴ ከተማን ለመፍጠር ሕዝቡን በማሳተፍ እና ባለድርሻ አካላትን በማነቃነቅ በተሰራው ውጤታማ ስራ አዲስ አበባ በአፍሪካ ውስጥ ካሉ 10 ፅዱ ከተሞች አንዷ ለመሆን መቻሏን አስገንዝበዋል።
ከተማዋ ከዚህ ቀደም በፅዱና ውብ አለመሆን እንዲሁም በአረንጓዴ ሽፋን ማነስ ትወቀስበት የነበረውን ገጽታ በኢትዮጵያ በኩል በተሰሩ ተከታታይ ስራዎች መቀልበስ መቻሉንም አብራርተዋል።
ፅዳት የዘወትር ስራና ባህል መሆን እንዳለበት የጠቆሙት ከንቲባዋ፣ በዕለት ተዕለት የሕይወት እንቅስቃሴ ውስጥ በሁሉም አካባቢ መረጋገጥ እንዳለበትም አሳስበዋል።

ፅዳት ከቤት እንደሚጀምር በመጥቀስም፣ ሁሉም ሰው በየአካባቢውና በየተቋሙ ይህንን ተግባር ባህል አድርጎ ሊይዘው እንደሚገባና ጉዳዩ ባህል እስኪሆን ድረስ ያለእረፍትና በትጋት በመስራት፣ ዘወትር ክትትል በማድረግ እያንዳንዱ ዜጋ የፅዳት አምባሳደር እንዲሆን አደራ ብለዋል።