ማኅበራዊ አክራሪነት መልክና ቅርጽ ይዞ ፖለቲካዊ ግብን ሲያነግብ፤ ወደ ፖለቲካዊ አክራሪነት ደረጃ ይሸጋገራል። ፖለቲካዊ አክራሪነት በአብዛኛው በፖለቲካ ልሂቃን የሚዘወር ሲሆን፤ ልሂቃን ኅብረተሰቡን በማንቀሳቀስ የፖለቲካ ግባቸውን ለማሳካት የሚጥሩበት አደገኛ መንገድ ነው።
በእሳቤ ደረጃ ፖለቲካዊ አክራሪነት በተማሪዎች እንቅስቃሴ ውስጥ ተወለደ ባይባልም፤ ከ1960ዎቹ ጀምሮ በነበረው ሶሻሊዝም በተጫነው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ጠንክሮ እንደወጣ አያጠያይቅም፡፡
አክራሪነት የፖለቲካ ባህላችን ዋነኛ መገለጫ እየሆነ ስለመጣ፤ የአክራሪነት ድርጊቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሱ፤ አክራሪነት የፖለቲካ ጨዋታው ገዥ ሕግ፤ መጠፋፋት ደግሞ ቀዳሚው መንገድ ሆኖ፤ ሕልውናችንን በከፋ የአደጋ አፋፍ ላይ አድርሰውታል።
ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተወራረሰ መጥቶም የጠንካራ ሀገር ግንባታ ዋነኛው ደንቃራ ሆኗል።
በሀገራችን ፖለቲካ ውስጥ የአክራሪነት መጠናከር ለለውጥና ለሀገር ግንባታ ፈታኝ የሆኑ ሦስት ተግዳሮቶችን ፈጥሯል። እነዚህም ሥር ነቀልነት፣ ደካማ ዴሞክራሲያዊ ባህል እና ደም አፋሳሽነት ወይም ያልዘመነ የትግል ስልት ናቸው።
ሥር ነቀልነት አንዱ የሠራውን እያረሙ በእርሱም ላይ የተሻለ ነገር እየጨመሩ ከመሄድ ይልቅ፤ አፍርሶ እንደገና የመጀመር ደካማ የፖለቲካ ባህል ነው።
ሀገራችንን ሠርከ አዲስ ጎጆ ወጪ እንድትመስል የሚያደርጋት ይህ አፍርሶ የመጀመር አባዜ ነው፡፡
የመደመር ትውልድ
ገጽ 55/56
