(የዕለቱ መልዕክት)
ዓለማችን በቴክኖሎጂ እና በኢኖቬሽን ፈጣን ግስጋሴ ውስጥ ትገኛለች። ኢትዮጵያም ይህንን ዓለም አቀፋዊ እውነት በውል በመገንዘብ፣ ሁለንተናዊ ኢኮኖሚዋን ከመሠረቱ የሚቀይር ታሪካዊ የዲጂታል ሽግግር እያከናወነች ትገኛለች።
በተለይም ባለፉት ዓመታት ሀገራችን ያለባትን ዘላቂ የቢሮክራሲ እና የኢኮኖሚ ፈተናዎች ለመቅረፍ ዲጂታላይዜሽንን እንደ ዋነኛ ስትራቴጂያዊ መሣሪያ በመውሰድ በቁርጠኝነት እየሠራችበት ነው።
ይህ ጉዞ የሀገርን የልማት ምሰሶ በጠንካራ መሠረት ላይ የሚያጸና የመንግሥት የረጅም ጊዜ ራዕይ ማሳያ ነው።
በአንድ ወቅት የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ እንደ ሩቅ ሕልም ይታይ የነበረ ቢሆንም በ“ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025” ስትራቴጂ በተከናወኑት መሠረታዊ ሥራዎች ዛሬ ውጤት መገኘት ችሏል።

አሁን ደግሞ የሀገራችንን የትራንስፎርሜሽን ጉዞ ይበልጥ የሚያፋጥን እና ይበልጥ ስኬታማ የሚያደርገው “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030” የተሰኘው ብሔራዊ ስትራቴጂ በትግበራ ላይ መዋሉ የሂደቱን ቀጣይነት ያረጋግጣል።
ከዚህ ጎን ለጎን የሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) በየተቋመት ጥቅም ላይ መዋል ለሚሰጠው አገልግሎት ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።
የ“ፋይዳ” ብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያ ፕሮግራምም ለጠቅላላው የዲጂታል ሥነ ምኅዳር ግንባታው መሠረት ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።
እስከ 90 ሚሊዮን ዜጎችን በሥርዓቱ ውስጥ ለማቀፍ የታቀደው ይህ ግዙፍ መርሐ ግብር ለባንክ፣ ለፋይናንስ፣ ለንግድ እንቅስቃሴ እና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ወሳኝ ምሰሶ ነው።

የሀገርን የሰው ኃይል በዕውቀት ሳያደራጁ ዘላቂ ስኬትን ማሰብ ስለማይቻል፣ ከዚህ መሠረት ጋር ተያይዞ በ“ኢትዮ ኮደርስ” ኢኒሼቲቭ 5 ሚሊዮን ዜጎች የዲጂታል ክህሎት ሥልጠና መጀመሩ የነገዋን የበለጸገች ኢትዮጵያ የሚረከቡ ባለሙያዎችን ለማፍራት የተጣለ ታላቅ መሠረት ነው።
ይህ የዲጂታል መሠረት የዜጎችን እንግልት ወደሚቀንስ የሲቪል ሰርቪስ ዝማኔ በተግባር ተሻግሯል።
የአገልግሎት አሰጣጥን በዘመናዊ መልክ ለመቅረጽ በሁሉም አካባቢዎች እየተገነባ የሚገኘው “የመሶብ” የአንድ ማዕከል አገልግሎት የተንዛዛ ቢሮክራሲን በማስቀረት የመንግሥትን ግልጽነት እና ተጠያቂነት በከፍተኛ ደረጃ አሳድጎታል።
ይህ ዓይነቱ የተቀናጀ አሠራር ሙስና እና ብክነትን በዘላቂነት ለመከላከል የሚያስችል አስተማማኝ ተቋማዊ አቅም እየፈጠረ ይገኛል።
በፋይናንስ ዘርፍም ቢሆን በዲጂታል የተከናወነው የግብይት ዋጋ 16 ትሪሊዮን ብር መድረሱ የዲጂታል ኢኮኖሚው ምን ያህል ውጤታማ እና ተደራሽ እየሆነ ለመምጣቱ ማሳያ ነው።
ይህ ስኬት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች እና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች በቀላሉ የብድር እና የቁጠባ አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ የፋይናንስ አካታችነትን በተግባር አረጋግጧል።
ለወደፊቱም መሠረታዊ የመንግሥት አገልግሎቶች ሙሉ በሙሉ በዲጂታል ፕላትፎርሞች ተደራሽ ለማድረግ የታቀደው ዕቅድ የሀገራችንን የነገ ገጽታ በእጅጉ የሚቀይር ነው።
መንግሥት የሳይበር ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ እና የስታርትአፕ ሥነ ምኅዳርን በማጠናከር፣ የዲጂታል ሽግግር ሂደቱን አስተማማኝ እና ደኅንነቱ የተጠበቀ እያደረገው ይገኛል።
ይህ ታሪካዊ ጉዞ የዜጎችን የዕለት ተዕለት ኑሮ የሚያቀልል፣ ሀገራችንን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚያደርግ እና የኢኮኖሚ ልማታችንን ከሕልም ወደ እውነት የለወጠ የጋራ ብሔራዊ ስኬታችን በመሆኑ ሁሉም አካላት ለስኬቱ የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ ይገባል።