በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ወቅት ድምጽ የሰጠው ሕዝብ፣ አሸናፊውን ፓርቲ የመረጠውም ሆነ ያልመረጠው፣ በምርጫው ላይ ሙሉ ተሳትፎ እንዳደረገ ሊወሰድ እንደሚገባ ተጠቁሟል።
በምርጫው ወቅት ማንኛውም ዜጋ ድምጹን የሰጠው የራሱን እይታ፣ መብትና ነጻነት ተጠቅሞ በመሆኑ፣ አሸናፊው ፓርቲ “ይህ መርጦኛል፣ ይህ ደግሞ አልመረጠኝም” በሚል ልዩነት ሊያደርግ እንደማይገባ የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኙ አቶ አብርሃም አብዲሳ ይገልጻሉ።
ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በአብላጫ ድምጽ የሚወሰንና የተሻለ ድምጽ ያገኘው አካል የሚያሸንፍበት ሥርዓት ቢሆንም፣ አሸናፊው ፓርቲ ግን መላውን ሕዝብ እንደመረጠው አድርጎ በተመሳሳይ መልኩ የማገልገል ኃላፊነት እንዳለበት አቶ አብርሃም ከኢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አማካሪ ፕሮፌሰር አድማሱ ገበየሁ በበኩላቸው፣ ምርጫን ተከትሎ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ የተዛቡ መረጃዎች የሀገርን ሰላም እና የዴሞክራሲ ሂደት አደጋ ላይ እንዳይጥሉ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
በዚህ ረገድ የሚዲያ ተቋማትና ይዘት አዘጋጆች ከማንኛውም አካል በላይ የላቀ ኃላፊነት እንዳለባቸው አመላክተዋል።
ከሀገር ውጭ በተለያዩ የማኅበራዊ ትስስር ዘዴዎች ከሚሰራጩ ሐሰተኛ መረጃዎችም ኅብረተሰቡ ሊጠነቀቅ እንደሚገባ ፕሮፌሰር አድማሱ አሳስበዋል።
እነዚህ አካላት ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ምርጫውን ለማጠልሸት የሚያደርጉትን ሴራ ማክሸፍ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።
ዴሞክራሲያዊ መብቱን ለመጠቀም ብርድና ፀሐይን ተጋፍጦ ድምጹን የሰጠው ሕዝብ፣ ውጤቱን ለማበላሸት የሚሞክሩ አካላትን የመታገል አቅም እንዳለው ተመላክቷል።
በመሆኑም ኅብረተሰቡ መረጃዎችን በጥንቃቄ በመመርመርና ሐሰተኛ መረጃዎችን በማጋለጥ የዜግነት ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ ቀርቧል።
በኢቢሲ ኤፍኤም አዲስ 97.1 ወቅታዊ ውይይት ላይ የተሳተፉት ፕሮፌሰር አድማሱ ገበየሁ እና አቶ አብርሃም አብዲሳ ለዴሞክራሲ መስዋዕትነት የከፈለው ሕዝብ፣ የሂደቱን ደህንነት የመጠበቅ ትልቁ አቅምና ስልጣን እንዳለው አስገንዝበዋል።
አሸናፊው ፓርቲ ሀገራችንን የሚመራ እንደመሆኑ መጠን፣ በሰላም እና ጸጥታ፣ የኢኮኖሚ ልማት የሀገር ግንባታ ላይ አተኩሮ ሊሰራ እንደሚገባ ተገልጿል።
በውይይቱ ላይ የተሳተፉ ዜጎችም ኢትዮጵያ መርጣለች፣ ኢትዮጵያ አሸንፋለች፤ ምርጫውን ለማደናቀፍ የተጉ ባንዳዎች እና ባዳዎች እንዳልተሳካላቸው በግልጽ ታይቷል፤ ይህም በኢትዮጵያ የባንዳዎች እና የባዳዎች ፀሐይ መጥለቋን በተግባር ያረጋገጠ ነው ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል።