የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ስትራቴጂ እና ስኬት ለአፍሪካ ምሳሌ እንደሚሆን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ክላቨር ጋቴቴ ገለጹ።
የአፍሪካ የልማት ተፅዕኖ ፎረም አዲስ አበባ በሚገኘው የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ቢሮ “ምርጥ ተሞክሮዎችን እና ፈጠራ የታከለበት መፍትሔ ለአፍሪካ የስራ ዕድል ፈጠራ” በሚል መሪ ሐሳብ እየተካሄደ ይገኛል።
ዋና ጸሐፊው በዚህ ወቅት እንደገለጹት፣ አፍሪካ የተፈጥሮ ሀብት፣ የፖሊሲ፣ የዕውቀት እና ከፍተኛ የሰው ኃይል እያላት በልማት ወደኋላ ቀርታለች።

የዓለም ነባራዊ ሁኔታ እና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የኢንዱስትሪውንና የሥራ ዕድል ፈጠራ ቅርፅን እየቀየረ መሆኑንም አንስተዋል።
የዓለም አቀፍ የልማት ፋይናንስ ድጋፍ እየቀነሰ በመሆኑ የአፍሪካ የወደፊት እጣ ፈንታ የራሷን ሀብት በመጠቀም፣ ኢንቨስትመንትን በማጠናከርና ዘላቂነት ያለውን የሥራ ዕድል በመፍጠር እንደሚወሰን አስገንዝበዋል።
የልማት ፖሊሲዎችን በጠንካራ ክትትል በመምራት ለውጤት ማብቃት የአፍሪካ የቤት ሥራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የኢንዱስትሪና የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ተሞክሮ የራስን ሀብት በመጠቀም ከፍተኛ ቁጥር ያለውን የሥራ ዕድል በመፍጠር እና የንግድ አድማስን በማስፋት ለአፍሪካ ምሳሌ እንደሚሆን ተናግረዋል።
በተጨማሪም የአፍሪካ ሀገራት ከሞሮኮ የአውቶሞቲቭ ዘርፍ፣ ከኬንያ የዲጂታል ኢኮኖሚ እንዲሁም ከሩዋንዳ ፈጠራ የታከለበት የሥራ ዕድል ፈጠራ ስኬት ልምድ በመውሰድ ፖሊሲዎችን መተግበር እንዳለባቸው ዋና ጸሐፊው አመልክተዋል።
በዛሬው ዕለት በተጀመረው የአፍሪካ የልማት ተፅዕኖ ፎረም ለሁለት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን፣ የፖሊሲ አውጭዎች፣ ወጣቶች እና የግሉ ዘርፍ ተዋናዮች እየተሳተፉ ይገኛል።
በባዬ ሙላት