የትግራይ ሰላም ኃይል ዋና አዛዥ ጄኔራል ገብረ እግዚአብሔር በየነ (ወዲ አንጥሩ) ወቅታዊውን የትግራይ እና የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሁኔታ አስመልክቶ ከኢቲቪ ትግርኛ ጋር በነበራቸው ቆይታ ጠንከር ያሉ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል።
ጄኔራሉ በሰጡት መግለጫ የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት አስፈላጊነት፣ የፌዴራሉን መንግሥት ቁርጠኝነት እና "ጽምዶ" የተባለውን ስብስብ በዝርዝር አብራርተዋል።
የፕሪቶሪያ ስምምነት የትግራይ ሕዝብ ጋሻ ነው፦ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ከማንም በላይ የትግራይን ሕዝብ ከጥፋት የታደገ ታሪካዊ ክስተት ነው ያሉት ጄኔራሉ፤ ትናንት በክፉ ቀን ቂማቸውን ሊወጡ የነበሩ ኃይሎችን ሴራ ያከሸፈ እና ቀጠናውን ወደ ሰላም የመለሰ ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል።
"ጽምዶ" የአኩራፊዎች እና የባንዳዎች ስብስብ ነው፦ ከሕወሓት ጋር በማበር ላይ የሚገኘው "ጽምዶ" የተባለው ስብስብ፣ ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ ፍላጎታቸው ያልተሳካላቸው የአኩራፊዎች እና በፖለቲካው ዓለም የከሰሩ እና የመጥፊያ ሰዓታቸው የደረሰ ኃይሎች ጥምረት ነው። ይህ ስብስብ የቀጠናውን ሰላም ለማወክ የተደራጀ "የባንዳ ስብስብ" ነው ሲሉም ጨምረው ገልጸዋል።
ይህ የጽምዶ ስብስብ ጊዜ ያለፈበት እና ኋላ ቀር ነው፦ ቡድኑ አሁን ካለው ዓለም አቀፋዊ የፖለቲካ አሰላለፍና እውነታ ጋር አብሮ የማይራመድ፣ ቆሞ የቀረ ስብስብ እንደሆነ ተናግረዋል።
"ሕወሓት የተባለውን ‘መዥገር’ ከሕዝቡ የመነጠል ጊዜው አሁን ነው" ያሉት ጄኔራሉ፣ በትግራይ ላይ በድጋሚ ጦርነት እንዳይቀሰቀስ እና የሕዝቡ ሰላም አስተማማኝ እንዲሆን፣ የትግራይ ሰላም ኃይል ከፌዴራል መንግሥት ጋር በቅንጅት እየሠራ እንደሚገኝም አረጋግጠዋል።
በአብርሃ ካሳ