ባለፉት አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ የቱሪዝም ልማት ላይ የተገኙት ውጤቶች የዘርፉን መዋቅር የቀየሩ እና በተጨባጭ መሬት ላይ የወረዱ ናቸው።
ቀደም ሲል የነበረውን የታሪክ እና የባህል ቱሪዝም ብቻ የመጠበቅ ልማድ በመስበር፣ አዳዲስ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ የቱሪስት መዳረሻዎች በከፍተኛ ጥራት ተገንብተው ለአገልግሎት በቅተዋል።
ታላላቅ የሀገር በቀል ሜጋ ፕሮጀክቶች፣ የኢኮ ቱሪዝም ማእከላት እና ደረጃቸውን የጠበቁ ፓርኮች ተጠናቅቀው ሥራ በመጀመራቸው ሀገራችን አዲስ የቱሪዝም አማራጭ ማቅረብ ችላለች።
ይህንን የመዳረሻዎች ልማት ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ የተከናወኑት የክልል አውሮፕላን ማረፊያዎች ግንባታ እና ማዘመን ሥራዎች፣ ቱሪስቶች በየክልሉ ያሉ ልዩ ተፈጥሯዊ ፀጋዎችን በቀላሉ ተንቀሳቅሰው እንዲጎበኙ በማድረግ ለዘርፉ ትስስር ትልቅ አቅም ፈጥረዋል።

በአዲስ አበባ እና በተለያዩ ክልሎች የተከናወኑት የኮሪደር ልማት እና የውበት ሥራዎች ከተሞችን ለቱሪስቶች ምቹ፣ ንጹህ እና ማራኪ አድርገዋቸዋል።
ይህም የውጭ ሀገር ቱሪስቶች እና ዲፕሎማቶች በከተሞች የሚኖራቸውን የቆይታ ጊዜ በእጅጉ በማራዘም የሆቴል፣ የምግብ እና የመጓጓዣ ዘርፉን ገቢ በከፍተኛ ደረጃ አሳድጎታል።
ሌላው ትልቅ ስኬት የውጭ ቱሪስቶችን ብቻ የመጠበቅን ባህል የቀየረው እና ዜጎች የገዛ ሀገራቸውን ውበት እንዲጎበኙ ያስቻለው የሀገር ውስጥ ቱሪዝም ማደግ ነው።
አዳዲሶቹ መዳረሻዎች ለሀገር ውስጥ ጎብኝዎች ክፍት በመሆናቸው ማኅበረሰቡ ሀገሩን እያደነቀ የመዝናናት ባህሉን እንዲያሳድግ እና በዘርፉ ላይ ያለው ባለቤትነት እንዲጠናከር አድርጓል።

የቱሪዝም ልማቱ በመዝናኛ ስፍራዎች ብቻ የተወሰነ ሳይሆን፣ መዳረሻዎቹ ለሚገኙባቸው ማኅበረሰብ አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን የፈጠረ ነው።
በሆቴል እና መስተንግዶ፣ በቅርስ እና የእጅ ሥራ ውጤቶች ሽያጭ፣ እንዲሁም በአስጎብኚነት ዘርፍ ለበርካታ ወጣቶች እና ሴቶች ዘላቂ የገቢ ምንጭ መፍጠር ተችሏል።
ይህም ቱሪዝምን ከማኅበረሰብ ጋር በቀጥታ በማስተሳሰር ከዘርፉ ተጠቃሚ አድርጓል።
ባለፉት አምስት ዓመታት በቱሪዝም ልማቱ የተመዘገቡት ውጤቶች የውጭ ምንዛሬ ከማስገኘት ባለፈ የኢትዮጵያን የሰላም፣ የዘመናዊነት እና የብልጽግና ጉዞ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተግባር የሚያሳዩ ትልቅ ስኬት መሆን ችለዋል።
በሔዋን ጌታቸው