የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሪያድ የሚገኘውን የኢፌዴሪ ሚሲዮን እና ጂዳ የሚገኘውን ቆንስላ ጽ/ቤት በማስተባበር ባደረገው የዲፕሎማሲ ጥረት በሳዑዲ ዓረቢያ ለእስር ተዳርገው የነበሩ 1 ሺህ 655 ዜጎቻችን የፍርድ ሂደታቸው ተቋርጦ የምሕረት አዋጅ እንዲሰጣቸው መደረጉን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አስታወቀ።
ይህ ውጤት መንግሥት በውጭ ግንኙነቱ ለዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ በሰጠው ትኩረት የተገኘ ነው ያለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ አኳያ በሳዑዲ ዓረቢያ ቀሪ የዲፕሎማሲ ጥረት የሚሹ ጉዳዮችን በተመለከተም ክትትል እያደረገ መሆኑን ጠቅሷል።
መንግሥት ኅብረተሰቡ ከሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች በማኅበራዊ ሚዲያ የታጀበ ሐሰተኛ ማታለያ ድርጊት የውጭ ሀገር ጉዞ ራሱን እንዲጠብቅም አሳስቧል።
ሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን የሕግ ተጠያቂ ለማድረግ የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አስታውቋል።