የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት የጋራ ኮሚቴ ቅንጅታዊ አሠራርን ማሻሻል እና ወደ አካታች ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የሚደረገውን ሂደት መከታተል በሚል መሪ ሐሳብ ግምገማዊ ውይይት አካሂደዋል።
የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት አቶ አሕመድ ሁሴን እና ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ተረፈ ደጌቲ በዚህ ወቅት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አጋርነቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ምክር ቤቱ ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤው እየተከናወኑ ያሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ለመድረኩ ተሳታፊዎች አቅርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
ምክር ቤቱ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤውን በተመለከተ ግንዛቤ የሚፈጥሩ መልዕክቶችን በመገናኛ ብዙኃን ተደራሽ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን አመላክቷል።
የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ኮሚሽኑ ከተቋቋመ ጀምሮ የጋራ መግባቢያ ሰነድ በመፈራረም በአጋርነት እየሠራ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜም ሀገራዊ ጉባኤው ላይ በማተኮር አጋርነቱን አጠናክሮ መቀጠሉን ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።