በትምህርት ዓለም የጽናትና የስኬት ትርጉም በብዙ መንገድ ይገለጻል።
የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተናን በዲላ ከተማ፣ በዳዊት የመጀመሪያና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የፈተና ማዕከል የወሰደችው የማንዴላ የርቀት ትምህርት አካዳሚ የርቀት ትምህርት ክፍል ተማሪዋ ወይዘሮ ትዕግሥት አለማየሁ ለመማር ያላትን ቁርጠኝነት በተለየ መንገድ አሳይታለች።
ፈተናው ሊጀመር ጥቂት ቀናት ወይዘሮ ትዕግሥት መንትያ ሴት ልጆችን በሚችሌ ጤና ጣቢያ በሰላም የተገላገለች ሲሆን፣ የወሊድ ሕመም ሳይበግራት፣ በተወለዱ በ11ኛ ቀናቸው ሁለቱንም ጨቅላዎቿን ይዛ በማዕከሉ በመገኘት ፈተናዋን ተፈትና አጠናቅቃለች።
ወይዘሮ ትዕግሥት፣ ከአዲሶቹ በተጨማሪ ሦስት ወንድ ልጆች እንዳሏት እና እነርሱም የ10ኛ፣ የ6ኛ እና የ4ኛ ክፍል ተማሪዎች መሆናቸውን ገልጻለች።
የነገ ሀገር ተረካቢ ልጆቿን ዝም ብላ ወደ ትምህርት ቤት ከመላክ ይልቅ ራሷም ጭምር በመማር ለእነርሱ መልካም አርአያ ለመሆን ስትል ለመማር መወሰኗን ትናገራለች።
የመማርን ፋይዳ የተገነዘበ ሰው ምንም ዓይነት የሕይወት ውጣ ውረድ ቢያጋጥመው ዓላማውን ከማሳካት ወደ ኋላ ማለት እንደሌለበት ትመክራለች።