Search

አየር መንገዱን ወደ ዓለም መሪነት የሚያሸጋግረው የአቡሴራው ሜጋ ፕሮጀክት

ዓርብ ሰኔ 12, 2018 77

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለፉት 80 ዓመታት የገነባው ገናና ስም በእውነተኛ የንግድ ስኬት እና ዘመናዊ የገበያ ስትራቴጂ ላይ የተመሠረተ ነው።

በአፍሪካ ቀዳሚ የሆነው አየር መንገዱ በዓለም አቀፍ ደረጃም ተወዳዳሪ ነው።

ይህ ስኬት የመጣው አህጉሪቱን እርስ በርስ እና ከዓለም ጋር በማገናኘት፣ በራሱ አካዳሚ የሠለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት እና ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ቀድሞ በመጠቀም ነው።

ተቋሙ "Vision 2010" እና "Vision 2025" ስትራቴጂያዊ ግቦቹን ከተቀመጠላቸው ጊዜ በፊት ማሳካቱ በዓለም አቀፍ አቪዬሽን ዘርፍ ታላቅ ክብርን አጎናፅፎታል።

SKYTRAX ሽልማት በተደጋጋሚ "የአፍሪካ ምርጥ አየር መንገድ" መባሉ እና የባለ 4 ኮከብ ደረጃን መያዙም የዚሁ ማረጋገጫ ነው።

የዓለማችን ትልቁ የአየር መንገዶች ጥምረት የሆነው ስታር አሊያንስ አባልነቱ ደግሞ ተደራሽነቱን ይበልጥ አስፍቶታል።

አሁን ደግሞ አየር መንገዱን ከአህጉራዊ የበላይነት ወደ ዓለም አቀፍ መሪነት የሚያሸጋግረው ታሪካዊ ፕሮጀክት በቢሾፍቱ አቡሴራ በከፍተኛ ፍጥነት እየተገነባ ይገኛል።

ይህ ሜጋ ፕሮጀክት ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ ከአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በአራት እጥፍ የላቀ የማስተናድ አቅም ይኖረዋል።

በዓመት እስከ 110 ሚሊዮን ተሳፋሪዎችን የማስተናገድ አቅም የሚኖረው ይህ አውሮፕላን ማረፊያ፣ አየር መንገዳችንን በዓለም ካሉ እጅግ ግዙፍ አየር ማረፊያዎች ተርታ ያሰልፈዋል።

አዲሱ የአቪዬሽን ከተማ ዲጂታል አሠራሮችን፣ ግዙፍ ቀረጥ ነፃ የገበያ ማዕከላትን፣ ሰፋፊ ማረፊያዎችን እና ዘመናዊ ሆቴሎችን ያካትታል።

ይህም ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የነበረበትን የቦታ ጥበት እና የአቅም ማነቆ ሙሉ በሙሉ የሚፈታ ነው።

የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደ ኢሚሬትስ እና ኳታር ካሉ ከፍተኛ የመንግሥት ድጋፍ ያላቸው አየር መንገዶች ጋር እንዲወዳደር እና የዓለም አቀፍ ተጓዦች ቀዳሚ ምርጫ እንዲሆን የሚያስችለው ነው።

በተጨማሪም አውሮፕላን ማረፊያው እጅግ ዘመናዊ የጭነት ተርሚናሎች ይኖሩታል።

ይህ መሠረተ ልማት ኢትዮጵያን የአፍሪካ የዲጂታል ንግድ (E-commerce) እና የግብርና ምርቶች ዋና ማዕከል ያደርጋታል።

በአጠቃላይ የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ የበረራ ብቃትን በማሳደግ የሥራ ማስኬጃ ወጪን የሚቀንስ ከመሆኑም በላይ፣ በሚቀጥሉት 50 ዓመታት የአየር መንገዳችንን የዓለም አቀፍ አቪዬሽን ተፅዕኖ ፈጣሪነት በተግባር የሚያረጋግጥ ታላቅ ስኬት ነው።

በንፍታሌም እንግዳወርቅ