Search

የ5ቱ ዓመታት ገጾች፦ የተፈጥሮ ሀብቶችን ወደ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች የቀየሩ የገበታ ፕሮጀክቶች

ሓሙስ ሰኔ 04, 2018 90

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተፈጥሮ፣ ታሪክ፣ ባሕል እና ሥነ-ምኅዳር ሀብቶች ከታደሉ ሀገራት መካከል ብትሆንም እነዚህን እምቅ ሀብቶቿን በተገቢው መንገድ አስተዋውቃ በመጠቀም ረገድ የሚጠበቅባትን ያህል ሳትሠራ ቆይታለች።

ለዚህም የመሠረተ ልማት እጥረት፣ የአገልግሎት ክፍተቶች እና የማስተዋወቅ ድክመቶች በርካታ የተፈጥሮ ሀብቶቿ ከአካባቢያዊ ዕውቀት ባለፈ ዓለም አቀፍ ትኩረት እንዳያገኙ አድርገዋል።

ይህንን ለመቀየር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) ሐሳብ አመንጪነት የተጀመሩ "ገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ" ፕሮጀክቶች ተፈጥሮን ከዘመናዊ መሠረተ ልማት ጋር በማጣመር አዲስ የቱሪዝም ምዕራፍ ከፍተዋል።

አዲስ አበባን ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋገረው የገበታ ለሸገር ፕሮጀክቶች፡-

በአዲስ አበባ የተገነቡ አብዛኛዎቹ ፕሮጀክቶች የገበታ ለሸገር ፕሮጀክት ውጤቶች ሲሆኑ፣ በቀደመው ጊዜ በከተማዋ የነበረውን ውስን የቱሪዝም መዳረሻ በማስፋት አሁን ተመራጯ ከተማ እንድትሆን አስችሏታል።

እንጦጦን ከጫካነት ባለፈ አስደናቂ የከተማዋ የቱሪዝም መዳረሻ ያደረገው እንጦጦ ፓርክ፣ ለሠርጎች እና ለአደባባይ ሁነቶች ተመራጭ የሆኑት አንድነት ፓርክ እና ወዳጅነት ፓርክ ለውጡ የወለዳቸው አዲስ አበባን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ያደረጉ የቱሪዝም መዳረሻዎች ናቸው።

የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክቶች፣ የኮሪደር ልማት ሥራዎች፣ የዓድዋ ሙዚየም፣ መስቀል አደባባይ እንደ አዲስ የተሠሩ እና የታደሱ ፕሮጀክቶች ሲሆኑ፣ ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎች አዲስ አበባን መዳረሻቸው እንዲያደርጉ የበኩላቸውን ሚና ተጫውተዋል።

የኢትዮጵያ ትልቁ ሐይቅ የሆነው ጣና ሐይቅ በተፈጥሮ ውበቱ ቢታወቅም የዓለም ደረጃ የቱሪዝም መዳረሻ ለመሆን የሚያስፈልጉ መሠረተ ልማቶች አልነበሩትም።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዐይን የጣናን ሐይቅ ውበት ለመግለጥ ማማተሩ የጎርጎራ ፕሮጀክት ዕውን እንዲሆን አስችሏል።

በሐይቁ ዳርቻ የተገነቡ ዘመናዊ ሆቴሎች፣ የመዝናኛ ማዕከላት፣ የእግረኛ መንገዶች፣ የጀልባ አገልግሎቶች እና የአረንጓዴ መስኮች የጣናን ውበት ከቀድሞው በተለየ መንገድ ለጎብኚዎች አቅርበዋል።

ዛሬ ጎርጎራ የጣናን ሐይቅ ውበት ብቻ ሳይሆን የአካባቢውን ታሪክ፣ ባህል እና ኢኮኖሚ የሚያሳይ መስኮት ሆኗል።

ወንጪ ሌላኛው በገበታ ፕሮጀክቶች ጎልቶ የወጣ ታሪካዊ ቦታ ነው።

ወንጪ ለብዙ ዓመታት በተፈጥሮ ፍቅር ያላቸው ሰዎች ዘንድ የሚታወቅ ቢሆንም በተገቢው መልኩ የተሟላ የቱሪዝም መዳረሻ አልነበረም።

በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት የተከናወኑ ልማቶች ግን የወንጪን ሐይቅ፣ ደሴቶቹን፣ የፍል ውኃ ምንጮቹን እና የተራራማው ገጽታ በተሻለ ሁኔታ በመሠራቱ ለቱሪስቶች አዲስ መዳረሻ ሆኗል።

በገበታ ፕሮጀክቶች ዐይን ውስጥ የገባችው ሌላኛው መዳረሻ ኮይሻ ስትሆን፣ በተፈጥሮ ውበቷ፣ በአረንጓዴ ሸለቆዎቿ እና በልዩ ሥነ-ምህዳሯ የምትታወቅ አካባቢ ናት።

በኮይሻ የተሠራው የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት በአካባቢው ያሉ የተፈጥሮ ሀብቶችን ሳይጎዳ ዘመናዊ የቱሪዝም መሠረተ ልማት በመገንባት የተፈጥሮ እና የልማት ሚዛን እንዴት ሊጠበቅ እንደሚችል ያሳየ ነው።

በአካባቢውም የሀላላ ኬላን ታሪካዊ ካብ ተከትሎ የተገነባው የሀላላ ኬላ ሎጅ እና ጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ ተከትሎ የተገነባው የዝሆን ዳና ሎጅ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ውጤቶች ናቸው።

በዚሁም ሀላላ ኬላ እና ጨበራ ጩርጩራ የኢትዮጵያን የዱር እንስሳት፣ የተፈጥሮ ደኖች እና ልዩ ሥነ-ምኅዳር ለዓለም ያስተዋወቁ መዳረሻዎች መሆን ችለዋል።

የገበታ ለትውልድ መርሐ ግብር የተገነባውና የአፋር ስጦታ የሆነው የኒዒን ፓልም ሎጅ የአካባቢውን ጸጋ የገለጠበት ሥራ ሲሆን፣ የቱሪዝም ልህቀት እና የግብርና ዘርፍ መነቃቃትን አዲስ ምዕራፍ በማብሰር፣ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ይበልጥ ጎልታ እንድትታይ የማድረግ ከፍተኛ ዐቅም አለው።

ሌላኛው በዚሁ መርሐ ግብር የተገናው የሸበሌ ሪዞርት መዝናኛ ስፍራ ብቻ ሳይሆን የዘመናዊ ሥነ-ሕንፃ ጥበብን ከሶማሌ ክልል ባሕላዊ እሴት ጋር አቀናጅቶ የያዘ የታሪክ ማኅደር በመሆን የቱሪዝም ከፍታን በማረጋገጥ ላይ ይገኛል።

ፕሮጀክቱ የለውጡ መንግሥት ኢትዮጵያን በአፍሪካ ቀዳሚ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የገባነውን ቃል በተግባር ያረጋገጠ የምሥራቁ የሀገራችን ክፍል ትልቅ ሥራ ነው።

እነዚህ ፕሮጀክቶች ከግንባታ በላይ ትርጉም ያላቸው እና የኢትዮጵያ ተፈጥሯዊ ሀብቶች ኢኮኖሚያዊ እሴት የሚያመነጩ እምቅ የቱሪዝም መዳረሻዎች እንደሆኑ በተግባር አሳይተዋል።

የቱሪስት ፍሰትን በመጨመር፣ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር፣ ለሆቴል፣ ለመጓጓዣ፣ ለዕደ ጥበብ እና ለሌሎች የአገልግሎት ዘርፎች ገቢ በማመንጨት ለአካባቢዎች እና ለሀገር ኢኮኖሚ ጉልህ አስተዋፅኦ እያደረጉም ይገኛሉ።

ከዚህም በላይ በአፍሪካ የቱሪዝም ካርታ ላይ የኢትዮጵያን ቦታ በማጠናከር ሀገራችን የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት ብቻ ሳትሆን ሀብቷን ወደ ዘላቂ ልማት ለመቀየር የምትችል ሀገር መሆኗን እያሳዩ ነው።

በዚህ ረገድ የገበታ ፕሮጀክቶች የመዝናኛ ስፍራዎች ብቻ ሳይሆኑ የኢትዮጵያን ውበት ለዓለም ያሳወቁ፣ የኢትዮጵያን ገጽታ ያሻሻሉ እና ቱሪዝምን ከኢኮኖሚ እድገት ጋር ያገናኙ የለውጥ ምልክቶች ሆነው ተቀምጠዋል።

በሀብተሚካኤል ክፍሉ