በአንድ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች፣ በልጅነትና በወጣትነት ዕድሜያቸው የሚጋሯቸው በጎና ክፉ አጋጣሚዎች፣ ዕድሎችና ውጣ ውረዶች ተመሳሳይ በመሆናቸው፣ ሰብዕናቸውና የሕይወት እይታቸው ተቀራራቢ መሆኑ አይቀሬ ነው ይላል የመደመር ትውልድ።
አካባቢያዊ፣ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ክስተቶችን አብሮ የመሻገር እውነታ የጋራ ማንነትን ይፈጥራል። በዚህ ሂደት ውስጥ ደግሞ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑ ግለሰቦች በትውልድ ቀረጻ ላይ ያላቸው ሚና እጅግ ከፍተኛ ነው።
ከስምንት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ምድር የለውጥ ነፋስ ሲነፍስ፣ ዕድሜያቸው በአሥራዎቹና ከዚያም በታች የነበሩ ታዳጊዎችን የአንድ አዲስ ዘመን ትውልድ ማሳያዎች ልንላቸው እንችላለን። ምንም እንኳ ገና የራሳቸውን የሕይወት ጎዳና መርጠው፣ የራሳቸውን ማኅበራዊ ምሕዳር ፈጥረው ጠባያቸውን በተሟላ መልኩ ባናውቀውም፣ ከእነርሱ በፊት ከነበረው ውል አልባ ትውልድ በብዙ እንደሚለዩ ግን አያጠራጥርም።
በዘመነ መደመር የተፈጠረው ይህ አዲስ ትውልድ፣ የኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካን መጻኢ ዕጣ ፈንታ የመወሰን ዕድል ያለው ነው፤ አገራችንና አህጉራችን በከፍተኛ የህልውና ፈተና ውስጥ ባሉበት ታሪካዊና ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መገኘቱም ለየት ያደርገዋል።
ይህንን አዲስ የመደመር ትውልድ በሚገባ ለመረዳት፣ አሁን ላይ እያሳየ ያለው ጠባይና በመደመር ሐሳብ ተኮትኩቶ ሊያንጸባርቃቸው የሚገቡትን ቀጣይ ባህርያት መመርመር ግን ያስፈልጋል።
በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ስዕል ውስጥ ዋናኛ ባለቤትና ተዋናይ የሆነው ይህ የመደመር ትውልድ ከቀደሙት ይልቅ ፍጹም የተለየ መሆኑ የታመነ ነው።
የመደመር ዘመን ኢትዮጵያ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት የላቀባት፣ የወንድማማችነትና የእኅትማማችነት እሴት የጸናባት፣ የሲቪክ ባህል የጎለበተበትና ቀጠናዊ ትስስር የጠነከረበት ማኅደር ለመሆን ጉዞ ጀምራለች።
ይህች አገር የምታሳየው ኅብረ ብሔራዊ አንድነት እውነተኛ ፌደራሊዝምን በተግባር የምታሳይ፣ ብዙኅ ማንነትን የምታቅፍና ብዙኃን ልሳናትን በክብር የምታስተናግድ ናት።
በዚህ ምድር ላይ ሌላውን እንደ ራሱ የሚመለከት፣ ብሔርንና አገራዊ ብሔረተኝነትን በውበት ያስታረቀ፣ የትናንቱን በጎ ቅርስ ይዞ የትናንቱን ሥህተት በይቅርታ የሚያርም፣ ትናንትን ከዛሬና ከነገ ጋር የሚያስማማ ንቁ ትውልድ እየተፈጠረ ነው።
በእነዚህ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ ስምምነት በማምጣት፣ አገራዊ መግባባትና ዘላቂ ዕርቅን የሚያሰፍን ትውልድ መፈጠሩ ተፈጥሯዊ ነው።
በእኩልነትና በመግባባት ላይ የተመሠረቱ የጋራና አስታራቂ ሕጎችን በመፍጠር የሚጓዙ ተቋማት፣ ለአገራችን አስተማማኝ ሰላምና ብልፅግናን ያረጋግጣሉ።
የጎረቤቶቿን ሰላምና ዕድገት እንደ ራሷ ዕድገት የምትመለከት፣ በጋራ የመልማትና አብሮ የመጓዝ ጥበብን የተላበሰች፣ በንግድና በሌሎች ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ጠንካራ ትስስር ለመፍጠር የምትተጋ፣ ቀጠናዊና አህጉራዊ ግንኙነቶቿን በመደመር ፍልስፍና የምትመራ አገር መገንባት ተጀምሯል።
የመደመር ትውልድ፣ የኢትዮጵያን ትልልቅ ሕልሞች እውን የሚያደርግና የዘመናት ምኞቷን ከማሳካት ጋር የተጣጣመ ሰብዕና ይኖረዋል። መለያ ባህርያቱ ከሆኑትና ወደፊትም በጉልህ ሊታዩ ከሚገባቸው እሴቶች መካከል፤ አዲስ ነገርን ለመማር፣ ለማወቅና ለመመራመር ያለው ጥልቅና እረፍት የሌለው ጉጉት እንዲሁም በምክንያትና በሐሳብ የበላይነት ላይ የተመሠረተ ጥልቅ የውይይት ባህል ግንባር ቀደሞቹ ተጠቃሽ ናቸው።