የቀይ ባሕር ቀጣና በአሁኑ ወቅት የዓለማችን ኃያላን ሀገራት ወታደራዊ እና የኢኮኖሚ በላይነታቸውን ለማረጋገጥ የሚሽቀዳደሙበት እጅግ ወሳኝ የስትራቴጂክ ማዕከል ሆኗል።
ከተለያዩ የዓለም ማዕዘናት የመጡ ሀገራት በቀጣናው ላይ የጦር ሰፈሮቻቸውን በመገንባት እና የባሕር ኃይላቸውን በማጠናከር ቀጣናውን የጥቅም ማስከበሪያ እያደረጉት ይገኛሉ።
ይህ የኃይል ሚዛን መለዋወጥ ደግሞ በቀጣናው እምብርት ላይ ለምትገኘው ኢትዮጵያ ቀጥተኛ ተፅዕኖ ያለው ጉዳይ እየሆነ መጥቷል።

በአፍሪካ በሕዝብ ቁጥር ሁለተኛ የሆነችው እና ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የምታስተዳድረው ኢትዮጵያ የራሷ የሆነ አስተማማኝና ቀጥተኛ የባሕር በር የላትም።
በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ለወደብ ኪራይና ለአገልግሎት የምታወጣው ኢትዮጵያ፣ ከባሕሩ ደጃፍ ላይ ቆማ የዓለም ንግድ እና ወታደራዊ እንቅስቃሴን ዝም ብላ እንድትታዘብ የሚያስገድዳት አንዳችም ምክንያታዊ ነገር የለም።

ከቀይ ባሕር በሺዎች በሚቆጠሩ ኪሎሜትሮች ርቀው የሚገኙ ሀገራት እየተሳቡ በመምጣት በቀጣናው ላይ ይዞታቸውን እያጠናከሩ ባሉበት በዚህ ወቅት፣ በቀጣናው ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ ወደብ አልባ ሆና እንድትቀጥል መደረጉ ፍፁም ፍትሃዊነት የጎደለው አካሄድ ነው።
ሌሎች ሀገራት ጥቅማቸውን ለማስከበር ወታደራዊ ቀጣና ሲያቋቆሙ ኢትዮጵያ የሕዝቦቿን የብልጽግና እና የደኅንነት ጥያቄ ለመመለስ የነበራትን ታሪካዊ የባሕር በር ለማስመለስ የምታደርገው ጥረት ተገቢ፣ ወቅታዊ እና ሊገታ የማይችል ነው።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ከባዶ ሜዳ የተነሳ ሳይሆን፣ ጠንካራ ታሪካዊ መሠረትና ዓለም አቀፋዊ ህጋዊ መርሆችን የተከተለ ነው።
ከታሪክ ባሻገር ዓለም አቀፍ ህጎች እና መርሆች ወደብ አልባ ሀገራት በድርድርና በሰላማዊ መንገድ የባሕር በር ማግኘት የሚችሉባቸውን ህጋዊ ማዕቀፎች ይፈቅዳሉ።
በመሆኑም ኢትዮጵያ ጥቅሟን ለማስከበር የምታደርገው ማንኛውም ዲፕሎማሲያዊና ህጋዊ ጥረት መብቷን የሚያስከብር እንጂ የሌሎችን ሉዓላዊነት የሚጋፋ አይደለም።
ኢትዮጵያ በቀጣናው ላይ ያላትን የባሕር በር ባለቤትነት መብት ለማስመለስ የምታደርገው ተከታታይ ስራ በሰላማዊ፣ በጋራ ተጠቃሚነት እና በዲፕሎማሲያዊ መርህ ላይ የተመሰረተ መሆኑ የሚታወቅ ነው።
በሃና ምንዳሁን