የኢትዮጵያ አየር ኃይል ለሀገራዊ ሉዓላዊነት እና ለሕዝባዊ ኩራት ዋስትና ሆኖ የቆመ፣ ዘመናትን የተሻገረ የታሪክ እና የጀግንነት ማማ ነው።
"ሰማዩ የኛ ነው" የሚለው የአየር ኃይሉ መሪ ቃል መፈክር ብቻ ሳይሆን፣ በጀግኖች አብራሪዎቻችን ደም እና አጥንት፣ በላቀ የአየር ላይ የበላይነት እንዲሁም ጥልቅ በሆነ የሀገር ፍቅር የተጻፈ እውነት ነው።

አንድ ክፍለ ዘመን የተጠጋ ዕድሜ ያለው የሰማዩ ንስር በአፍሪካ ሰማይ ሥር ያስመዘገበው ደማቅ ታሪክ፣ ሀገራችን ያጋጠሟትን የሕልውና አደጋዎች ሁሉ በድል እንድትወጣ አድርጓል።
በተለያዩ የፖለቲካ ሥርዓቶች ውስጥ አኩሪ ገድል የፈጸመው አየር ኃይላችን፣ ዛሬ ላይ ዘመኑን የሚመጥን የላቀ አደረጃጀት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ ደርሷል።
በጀግንነት የታተሙ የታሪክ አሻራዎች
አየር ኃይሉ በትናንትናው ታሪኩ ኢትዮጵያ ላይ የተቃጡ የወረራ ሙከራዎችን በመመከት ረገድ የማይተካ ሚና ተጫውቷል። በ1969 ዓ.ም የዚያድ ባሬ ጦር በሀገራችን ላይ የከፈተውን ወረራ በብቃት አምክኗል።
ያኔ አየር ኃይላችን የታጠቃቸው መሣሪያዎች በቁጥርም ሆነ በዘመናዊነት ከጠላት ትጥቅ ጋር የማይመጣጠኑ ቢሆኑም፣ በF-5E ተዋጊ ጄቶች የጠላትን 13 ሚግ-17 (MiG-17) እና 12 ሚግ-21 (MiG-21) አውሮፕላኖችን በአየር ላይ በማስቀረት ፍጹም የበላይነትን ተቀዳጅተዋል።
በዚህ ታሪካዊ ውጊያ ላይ እንደ ጄኔራል ለገሠ ተፈራ፣ ኮሎኔል ባጫ ሁንዴ እና ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ ያሉ ጀግኖች አብራሪዎች የአየር ላይ ፍልሚያ ብቃታቸውን በተግባር በማሳየት የጠላትን ቅዠት ከንቱ አስቀርተውታል።
በተመሳሳይ መልኩ ለሰባት ዓመታት ዝግጅት አድርጎ (1991 - 1993 ዓ.ም) ኢትዮጵያን የወረረውን የሻዕቢያ ጦርነት በመቀልበስ ረገድ የአየር ኃይሉ ሚና እጅግ ከፍተኛ ነበር። ያ ጦርነት በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሶቪየት ምርት የሆኑት ሱ-27 (Su-27) እና ሚግ-29 (MiG-29) አውሮፕላኖች ፊት ለፊት በተፋለሙበት የአየር ላይ ውጊያ የሚታወስ ነው። የኢትዮጵያ ሱ-27 ተዋጊዎች የጠላትን ሚግ-29 አውሮፕላኖች ከጥቅም ውጭ በማድረግ ፍጹም የአየር የበላይነታቸውን አስመስክረዋል።
ጀግኖቹ የኢትዮጵያ አብራሪዎች ጠላት አለኝ የሚላቸውን ምርጥ አብራሪዎች እና ጄቶች እንደ ጉም በማትነን ኢትዮጵያ የማትደፈር መሆኗን ዳግም አረጋግጠዋል።
መዋቅራዊ ፈተና እና ዳግም ትንሣኤ
ይህ ታላቅ ተቋም እዚህ የደረሰው አልጋ በአልጋ በሆነ መንገድ ሳይሆን የገጠሙትን ከፍተኛ መዋቅራዊ እና ፖለቲካዊ ፈተናዎችን በጽናት በማለፍ ነው።
የ1983 ዓ.ም መዋቅራዊ ድቀት፦ የሥርዓት ለውጡን ተከትሎ የቀድሞው ሠራዊት ሙሉ በሙሉ እንዲበተን በመደረጉ አየር ኃይሉም ከባድ መዋቅራዊ ድቀት አጋጥሞት ነበር።
በርካታ በውጭ ሀገር የሠለጠኑ፣ ከፍተኛ የቴክኒክ እና የበረራ ብቃት የነበራቸው አንጋፋ አብራሪዎች እና መሐንዲሶች ከሥራ ሲገለሉ፣ አብዛኞቹም ለእስራት እና ለስደት ተዳርገዋል። ይህ መዋቅራዊ መዳከም ተቋሙን ከፍተኛ የሰው ኃይል እጥረት ውስጥ የከተተው ቢሆንም፣ የድንበር ጦርነት ተከፍቶ የሕልውና አደጋ ሲደቀን ግን የሰማይ ንስሮቹ ወደ ኋላ አላሉም።
ለእስር እና ለእንግልት ተዳርገው የነበሩት የኢትዮጵያ አብራሪዎች የደረሰባቸውን በደል ወደ ጎን በመተው፣ ለሀገር ሉዓላዊነት ሲሉ ሁሉንም ትተው ግዴታቸውን ተወጥተዋል።

ተቋሙ እስከ 2010 ዓ.ም ለውጥ ድረስ ኢትዮጵያን ከሚመጥን ደረጃ ወርዶ በጥቂት ተዋጊዎች ብቻ እስከ መቅረት የደረሰ መዋቅራዊ መዳከም ደርሶበት ቆይቷል።
የዘመናችን የቴክኖሎጂ ማማ እና የነገው ራዕይ
ዛሬ ላይ ግን የኢትዮጵያ አየር ኃይል የቢሾፍቱን ታሪካዊ ጠቅላይ መምሪያ በዘመናዊ መልክ በማደስ እና በማስፋፋት፣ ካለፉት ጊዜያት በላቀ ጥንካሬ እና ዘመናዊ መዋቅር በተጠንቀቅ ላይ ይገኛል።
በቅርቡ በተከበረው የ90ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉ ላይ በይፋ እንደተገለጸው አየር ኃይሉ የ4ኛ ትውልድ (4th Generation) ተዋጊ አቅም ላይ ደርሷል።
በአሁኑ ወቅት ሁለገብ ተዋጊ የሆኑትን ዘመናዊ ጄቶችን፣ የላቁ የውጊያ እና የማሠልጠኛ አውሮፕላኖችን እንዲሁም ዘመናዊ ሰው አልባ ተዋጊዎችን ታጥቆ የአየር ክልላችንን ነቅቶ በመጠበቅ ላይ ይገኛል።
ሀገራችን በወታደራዊ ቴክኖሎጂ ራስን የመቻል ስትራቴጂን በመከተል ትልቅ እርምጃ እየተራመደች ትገኛለች።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተመረቁት "ስካይዊን ኤሮኖቲክስ ኢንዱስትሪ" እና "ኤይሮ ዓባይ" የተባሉ የሀገር ውስጥ የድሮን ማምረቻ ተቋማት የዚህ ጥረት ሕያው ምስክሮች ናቸው።
በእነዚህ ማዕከላት የሚመረቱ ሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) የአየር ክልል እና የድንበር ደኅንነትን ለመቆጣጠር የቅኝት እና መረጃ ማሰባሰብ፣ የታለመ ዒላማ በመምታት የፀረ-ሰላም ኃይሎችን ስምሪት ማክሸፍ፣ እንዲሁም እንደ ግብርና እና መሠረተ ልማት ጥበቃ ላሉ የሲቪል አገልግሎቶች የሚውሉ ናቸው። ይህ ስኬት ኢትዮጵያን ከድሮን ገዢነት ወደ ቴክኖሎጂ አምራችነት በከፍተኛ ፍጥነት እያሸጋገራት ይገኛል።
የማይነቃነቀው የኢትዮጵያ የደኅንነት ጋሻ
ይህ የቴክኖሎጂ፣ የመሠረተ ልማት እና የሰው ኃይል ግንባታ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ታላቅ አቅም የፈጠረ ሲሆን፣ ይህም የሀገራችንን ታሪካዊ ተገዳዳሪዎች ከፍተኛ ፍርሃት እና ድንጋጤ ውስጥ የከተተ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አሁንም ድረስ ጊዜ ባለፈባቸው ቴክኖሎጂዎች የኢትዮጵያን ታላቅነት እና ሉዓላዊነት ለመገዳደር ለሚያስቡ ኃይሎች ጥብቅ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ኢትዮጵያ አሁን በክፉ የሚስቧትን እና የሚተነኩሷትን በዝምታ የምታልፍ ሳትሆን፣ ሉዓላዊነቷን የደፈሩ ኃይሎችን በሰማይም ሆነ በምድር አሳድዳ የምትቀጣ እና እርምጃ የምትወስድ ኃይል ሆናለች።
ለቀጣይ የብልጽግና ጉዟችን አየር ኃይሉ በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት የተዋጊ አውሮፕላኖቹን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ለማሳደግ እና ወደ 5ኛ ትውልድ (5th Generation) የጦር ጄት ቴክኖሎጂ ሙሉ በሙሉ ለመሸጋገር በትኩረት እየሠራ ይገኛል።
ይህ ወታደራዊ ዝግጅት ከሀገራችን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው። የአየር ኃይሉ ጥንካሬ የምሥራቅ አፍሪካን የኃይል ሚዛን ሙሉ በሙሉ በማስጠበቅ የኢትዮጵያን ቀጣናዊ የበላይነት እና ሰላም የሚያረጋግጥ የአስተማማኝ ደኅንነት ጋሻ ሆኖ ይቀጥላል።
በለሚ ታደሰ