ዛፍ መትከል የሕልውና ጉዳይ መሆኑን፣ የቢሊዮን ዶላሮች የኢኮኖሚ ምንጭ በመሆን ጭምር እያረጋገጠ ይገኛል።
የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብርም ከችግኝ ተከላ ዘመቻነት አልፎ፣ ሀገራችንን ወደ አዲስ የኢኮኖሚ እና የዲፕሎማሲ ምዕራፍ እያሸጋገራት ነው።
የዓለማችን የአየር ንብረት ለውጥ ፈጣን እና አሳሳቢ እየሆነ በመጣበት በዚህ ዘመን፣ ኢትዮጵያ ታሪካዊ የሆነ የደን መመናመንን ለመቀልበስ ሰፊ እርምጃ ወስዳለች።
በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር እስካሁን ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን ተክለናል፤ ከእነዚህም ውስጥ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ያላቸው የፍራፍሬ፣ የቡና እና ሌሎች የዛፍ ዓይነቶች ይገኙበታል።
ይህ መርሐ ግብር ከችግኝ ተከላ የዘለለ ግዙፍ ዓለም አቀፋዊ የኢኮኖሚ ትርጉም ያለው ሲሆን፣ የካርበን ሽያጭ በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ነው።
የካርበን ሽያጭ ማለት በአጭሩ፤ በአረንጓዴ ዐሻራ የሚተከሉት ቢሊዮን ዛፎች ከፍተኛ መጠን ያለው ካርበን ከከባቢ አየር ውስጥ ይመጥጣሉ፤ በካይ ሀገራት ደግሞ ለዚህ የተፈጥሮ ውለታ ክፍያ የሚፈጽሙበት ሥርዓት ነው።

በዚህም ኢትዮጵያ ተጨባጭ ስኬቶችን አስመዝግባለች። በሁምቦ እና ሶዶ ማኅበረሰብ አቀፍ የደን ልማት፣ ሙሉ በሙሉ ተራቁተው የነበሩ ተራሮች አገግመው ማኅበረሰቡ ከዓለም ባንክ "የካርበን ፈንድ" የገንዘብ ተጠቃሚ መሆን ችሏል።
በኦሮሚያ የደን ገጽታ ፕሮጀክትም፣ የክልሉን ደኖች ያካተተ እና በውጤት ላይ የተመሠረተ ክፍያ የሚያስገኝ ግዙፍ ሥራ ነው።
በሌላ በኩል፣ ኢትዮጵያ ችግኝን እንደ ዲፕሎማሲያዊ መሣሪያ እየተጠቀመችበት ትገኛለች። ለጎረቤት ሀገራት ጅቡቲ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ እና ደቡብ ሱዳን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በነጻ በማካፈል "የአረንጓዴ ቀበቶ" ራዕይን እውን እያደረገች ነው።
ከዚህም ባለፈ፣ የዛፎች መተከል አፈር መሸርሸርን በመከላከል፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦችን ከደለል እየታደገ ይገኛል።

የዚህ ሁሉ ስኬት ምስጢር የማኅበረሰቡ የባለቤትነት ስሜት ነው። በዚህም ዛፍ መትከል የዝናብ ዑደትን እንደሚያስተካክል የተገነዘበው ማኅበረሰቡ፣ ችግኞችን በመንከባከብ ረገድ ከፍተኛውን ሚና በመጫወት፣ በየዓመቱ የሚተከሉ ችግኞች የመጽደቅ ምጣኔ ከ80 በመቶ በላይ መሆን ችሏል።
የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ትርፍ ዘላቂ እንዲሆን የዘርፉ ባለሙያዎች ሦስት ዋና ዋና ነጥቦችን ያነሣሉ፦
የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ ጸድቀው ዛፍ መሆናቸውን ማረጋገጥ፣ ኅብረተሰቡ የችግኞቹ ቀጥተኛ ጠባቂ እና ተጠቃሚ የሚሆንበትን አሠራር ማጠናከር፣ እና የካርበን ሽያጭ ተቋማዊ አሠራሮችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማገዝ፣ ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ፋይናንስ ተገቢውን ክፍያ እንድታገኝ አጠናክሮ መሥራት የሚሉት ናቸው።
በሲሳይ ደበበ