(የዕለቱ መልዕክት)
ቴክኖሎጂ በረቀቀበትና ዓለም አቀፋዊ ፉክክር በጠነከረበት በዚህ ዘመን፣ ያለ ትምህርት ጥራት ሁለንተናዊና ዘላቂ ብልጽግናን ማረጋገጥ በፍጹም አይቻልም።
ትምህርት የዕውቀት መቅሰሚያ ብቻ ሳይሆን የማኅበረሰብን የወል ትርክት መፍጠሪያ፣ ብሔራዊ መግባባትን መገንቢያና የሀገርን ሕልውና ዘላቂ የማድረጊያ ዋና ድልድይ ነው።
በዘርፉ ላይ የታዩ ታሪካዊና መዋቅራዊ ስብራቶችን ለመጠገን ላለፉት አምስት ዓመታት የተወሰዱት እርምጃዎችና የተመዘገቡት ስኬቶች፣ ኢትዮጵያ ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋን ለመቅረጽ የጀመረችውን ስልታዊ ሽግግር በግልጽ ያሳያሉ።
ለ28 ዓመታት የቆየውን አሮጌ ፖሊሲ በመቀየር፣ አዲስ የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታን መሠረት ያደረገ ፖሊሲ ወደ ትግበራ መግባቱ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ከፍቷል።
ይህ ማሻሻያ ለመጀመሪያ ጊዜ የአጠቃላይ ትምህርት አዋጅና የብቃት ማዕቀፍ ሥርዓት እንዲዘረጋ በማድረግ ረገድ ትልቅ መሠረት መሆኑ ይታመናል።
ለትምህርት ዘርፉ የተሰጠው ይህ ከፍተኛ ቁልፍ ትኩረት፣ አሰልቺና ንድፈ ሐሳባዊ ብቻ የነበረውን አሠራር በመስበር በተግባር የታገዘና ተጨባጭ ውጤት ማምጣት የቻለ ስትራቴጂካዊ እርምጃ ነው።
በትምህርት ተደራሽነትና ጥራት ዙሪያም የተከናወኑ መዋቅራዊ ለውጦች በርካታ ዐበይት ምሰሶዎችን ያካትታሉ።
በ"ትምህርት ለትውልድ" ንቅናቄ አማካኝነት የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻልና የመሠረተ ልማት ግንባታን የማፋጠን ሥራ የተከናወነ ሲሆን፣ በተለይም ዓለም አቀፍ አድናቆት ያተረፈው የትምህርት ቤት ምገባ መርሐ ግብር ከ8 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን መመገብ አስችሏል።
ይህ ስልታዊ እርምጃ ተማሪዎች በትምህርታቸው እንዲገፉና የማቋረጥ ምጣኔው እንዲቀንስ በማድረግ፣ ለብዙ ወላጆች ትልቅ ማኅበራዊ እፎይታን ከመስጠቱም በላይ ለትምህርት ጥራት መሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል።
ከዚህ ጎን ለጎን ትምህርትን ከተጨባጭ የሀገር እውነታ ጋር ለማገናኘት ሀገር በቀል ዕውቀት በሥርዓተ ትምህርቱ ውስጥ እንዲካተት መደረጉ፣ እንዲሁም "ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025" አጀንዳን መሠረት በማድረግ በርካታ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በኮምፒውተር ላብራቶሪና በኢንተርኔት መገናኘታቸው ለትምህርት ጥራት ሌላኛው መፍትሔ ተደርጎ ይወሰዳል።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ጥራትና ብቃት ለመለካት የዩኒቨርሲቲ መውጫ ምዘና (Exit Exam) ተግባራዊ መደረጉ በንድፈ ሐሳብና በተግባር መካከል ያለውን ክፍተት የደፈነ ቁልፍ እርምጃ ነው።
ይህ የፈተና ሥርዓትና የተዘረጋው የቁጥጥር ማዕቀፍ፣ ለአሥርት ዓመታት የአካዳሚክ ታማኝነትንና የትውልዱን የሥነ ልቦና መዋቅር ሲያናጋ የኖረውን የኩረጃ መጥፎነትና አውዳሚነት ለመግታት የተወሰደ ታሪካዊ እርምጃ ነው።
ኩረጃ የራስን አቅም አሳንሶ የመመልከትና የሌሎችን ጥረት በመስረቅ ሀገርንና ትውልድን የማታለል ትልቅ የሞራልና የማኅበረሰብ ውድቀት ነው። ኩረጃ ባለበት ቦታ እውነተኛ ዕውቀትና የፈጠራ ብቃት ሊበቅል አይችልም፤ ሀገርም በትክክለኛ ባለሙያዎች እጅ አትወድቅም።
ስለሆነም ይህንን አጥፊ ልማድ በቆራጥነት መዋጋትና የልፋትን ዋጋ የሚያስከብር ፍጹም የብቃት ሥርዓት መገንባት ከተመዘገቡት ውጤቶች ሁሉ የላቀ ስኬት ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል።
ዩኒቨርሲቲዎች በተልእኮ እንዲለዩና ወደ ራስ ገዝነት እንዲሸጋገሩ ሥርዓት መዘርጋቱም ይህንን ከኩረጃ የነጻ ተወዳዳሪ የሰው ኃይል የማፍራት ሂደት ይበልጥ ያረጋግጠዋል።
እስካሁን የተመዘገቡት ስኬቶች የሚደነቁና በትኩረት የተገኙ ቢሆኑም፣ ወደፊት የሚጠብቀን ጉዞ ግን የላቀ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የማያቋርጥ ክትትልን፣ ቀጣይነት ያለው ሥራንና መጠነ ሰፊ ኢንቨስትመንትን የሚጠይቅ ነው።
የትምህርት ጥራትን ማሻሻል የአንድ ጊዜ ዘመቻ ወይም የአጭር ጊዜ ፕሮጀክት ሳይሆን፣ የማያቋርጥ የሀብት በጀት መድቦ በትጋት መሥራትን የሚጠይቅ የረጅም ጊዜ ብሔራዊ ኢንቨስትመንት ነው።
የመማሪያ ቁሳቁሶችን ማሟላት፣ የነፍስ ወከፍ መጻሕፍት ተደራሽነትን ማረጋገጥ፣ የአስተማሪዎችን ሙያዊ ብቃት ማሳደግ እንዲሁም ዘመናዊ መሠረተ ልማቶችን በየደረጃው መገንባት ቀጣይነት ያለው ከፍተኛ የፋይናንስና የሰው ኃይል ኢንቨስትመንት ይሻል።

የነገው የሀገራችን ስትራቴጂያዊ አቅጣጫ በ"ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" ማዕቀፍ ውስጥ ሰው ሠራሽ አስተውሎትን (AI) በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ በስፋት ማካተት በመሆኑ፣ በሰው ኃይል ሥልጠና፣ በሥርዓተ ትምህርት ዝግጅትና በመሠረተ ልማት ማሟላት ላይ በግንባር ቀደምትነት መረባረብ ያስፈልጋል።
እንደ ሀገር ትምህርትን የነገ ተስፋችን ማለሚያ ቁልፍ መሣሪያና ለብሔራዊ የትውልድ ግንባታ ተልእኮ አድርገን በመውሰድ፣ መላው ማኅበረሰብ፣ የግል ባለሀብቶችና የትምህርት ባለሙያዎች በባለቤትነት ስሜትና በተግባራዊ ድጋፍ ሊረባረቡ ይገባል።
የሀገራችን ሁለንተናዊ ልማት፣ ኢኮኖሚያዊ ጥንካሬና ብሔራዊ ሉዓላዊነት አስተማማኝ በሆነ ጽኑ መሠረት ላይ ሊቆም የሚችለው በኩረጃና በሐሰት ሳይሆን በእውነተኛ ዕውቀቱ፣ በታማኝ ስብእናውና በላቀ የፈጠራ ብቃቱ የጸና ትውልድ ሲገነባ ብቻ ነው።
የኢቢሲ ዶትስትሪም ኤዲቶሪያል