Search

ዛሬ በእጃችን የተተከለ፣ ነገ ለትውልድ የሚተርፍ አረንጓዴ ቅርስ

ሓሙስ ሰኔ 11, 2018 34

አረንጓዴነት የውበት መገለጫ ብቻ ሳይሆን የሕይወት ቀጣይነት ዋስትና በመሆኑ ዛሬ በእጃችን የምንተክለው ችግኝ ነገ አድጎና አፍርቶ ለቀጣዩ ትውልድ የሚተርፍ እምቅ ሀብት ይዞ ይመጣል።
ይህ በየደረጃው የሚገኘውን ማህበረሰብ ያሳተፈው ብሔራዊ ንቅናቄ፤ ህጻናት፣ ወጣቶችና አረጋውያን በአንድነት ወጥተው አፈር ሲዳስሱና ችግኝ ሲተክሉ የአገር ፍቅር ስሜት በተግባር የሚገለጽበትን ህያው ምስል ይፈጥራል።
እያንዳንዷ በእጅ የምትቆፈር ጉድጓድና የምትተከል ችግኝ የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ጋር ያለውን ትስስር የምታድስ ከመሆኗም በላይ የተራቆቱ ተራሮችን መልሶ ለማልማት፣ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እና ለተተኪው ትውልድ ለምለም ምድርና ንጹህ አየር ለማስረከብ የተጀመረው ብሔራዊ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በትክክልም ትልቅ ለውጥ ማምጣት ችሏል።
ባለፉት ዓመታት በይፋ የተጀመረው ይህ ታሪካዊ ንቅናቄ በኢትዮጵያ በተስተዋለው የደን መራቆት ሳቢያ የተከሰቱ የአፈር መሸርሸርና የድርቅ ተጽዕኖዎችን ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተ ሲሆን በአጭር ጊዜ ውስጥም መላውን ሕዝብ ያሳተፈ ብሔራዊ ንቅናቄ መሆን ችሏል።
 
በተለይም ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በየዓመቱ ከዳር እስከ ዳር በመውጣት ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል በዓለም አቀፍ ደረጃ ትኩረትን የሳበ ታሪካዊ ክንውን ፈጽሟል።
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በአንድ ዓመት የተገደበ ዘመቻ ሳይሆን “አረንጓዴ ዐሻራችን ለትውልዳችን”፣ “በመትከል ማንሰራራት” እና “የምትተክል ሀገር፣ የሚያጸና ትውልድ” የሚሉ መሪ ቃላትን በመቅረጽ በየዓመቱ ይዘቱን እያሰፋ ቀጥሏል።
ይህ ታሪካዊ ንቅናቄ ከቀላል የችግኝ ተከላ ዘመቻ ባለፈ ዘላቂ ኢኮኖሚያዊና አካባቢያዊ ግቦችን ያነገበ ሲሆን ከተተከሉት ችግኞች መካከል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ተክሎች በመሆናቸው የምግብ ዋስትና ከመስጠት ባለፈ ለገበያ እና ለገቢ ምንጭነትም እየዋሉ ይገኛሉ።
በመሆኑም ዛሬ በእጃችን የተተከለው ችግኝ ነገ ፍሬ አፍርቶ ለእኛም ሆነ ተተኪው ትውልድ የሚወርሰው ሀብት በነሆኑ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ ተሞክሮ ከሀገር አልፎ ለዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ተግዳሮቶች መፍትሄ ሊሆን የሚችል ትልቅ ተነሳሽነት ፈጥሯል።