Search

የሃሳብ ፖለቲካ ታጋዮች እና የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ አዲስ ልደት

ሰኞ ሰኔ 15, 2018 96

ባለፉት 10 ዓመታት በሀገራችን የተካሄዱ ምርጫዎች አብዛኛውን ጊዜ በውጥረት፣ በስጋት እና በወቅታዊ የኃይል ፉክክር ማዕቀፍ ውስጥ የሚቃኙ ነበሩ።

ይሁን እንጂ የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ፍጻሜውን ሲያገኝ የታሪኩ ማጠንጠኛ ከተለመደው የፖለቲካ ውድድር አጥር ወጥቶ የሀገርን ሕልውና እና ሉዓላዊነት በተግባር የማረጋገጫ ትልቅ የታሪክ እመርታ ሆኖ ተመዝግቧል።

ይህ ምርጫ በውጫዊ ጫናዎችና በውስጥ ውስብስብ የሴራ መረቦች የተከበበ ቢሆንም ኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ በራሷ ሁለንተናዊ አቅም፣ ያለ ምንም የውጭ ጣልቃገብነት ያከናወነችው ታሪካዊ ክንውን ሆኗል።

ሂደቱ በራሱ የሀገር በቀል ዴሞክራሲን ጥንካሬ ያሳየበት እና ለአህጉራዊ ሉዓላዊነት ዋስትና መሆኑን ለመላው አፍሪካ  የኩራት ተምሳሌት ነው።

ይህ ታሪካዊ ምዕራፍ ትናንትን በማከም እና ነገን በፅኑ መሠረት ላይ በመተለም የተጀመረው የከፍታ ጉዞ የታየበት ልዩ መድረክ ነው።

የምርጫውን ስኬት የገነባውና ዋና የጀርባ አጥንት የሆነው ደግሞ በሂደቱ ውስጥ የተሳተፉት 42 ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከ10 ሺህ በላይ ዕጩ ተወዳዳሪዎች ያሳዩት ስልጡን የፖለቲካ ቁርጠኝነት ነው።

ከውስጥም ከውጭም ይነፍስ የነበረውን የሀሰት ወጀብና የተዛባ ፕሮፓጋንዳ በፅናት በመቋቋም፣ ለሰላማዊ የሃሳብ ውድድር እና ለሕግ የበላይነት የቆሙት እነዚህ አካላት፣ ሕዝቡ አማራጮችን በሰፊው መዝኖ በነጻነት እንዲመርጥ ትልቅ ዕድል ፈጥረዋል።

የፖለቲካ ብስለትን በተግባር ያሳዩት እነዚህ ተፎካካሪዎች፣ ከተለመደው ዋልታ ረገጥነት የሃሳብ የበላይነት ማመን እንደሚቻል አረጋግጠዋል።

ለዴሞክራሲያዊ ተቋማት ማደግና ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል ማበብ ታላቅ መሠረት የጣሉ፣ የሕዝብ ሉዓላዊነት አክባሪዎችና የሃሳብ ፖለቲካ ታጋዮች በመሆናቸውም ክብርና እውቅና ይገባቸዋል።

ይህ አዲስ ምዕራፍ ኢትዮጵያ በማንኛውም ውጫዊ ጫና ሳትበገር የራሷን ዕድል በራሷ የመወሰን ብስለትና አቅም እንዳላት በተግባር ያስመሰከረችበት ታላቅ የታሪክ እመርታ ነው።

በበረከት ሽመልስ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: