Search

ኢትዮጵያውያን በሰለጠነ የውይይት ባህል ታሪክን የሚያሻግር አዲስ ማኅበራዊ ውል አጸደቁ

እሑድ ነሐሴ 17, 2018 96

በኢትዮጵያ የፖለቲካና ማኅበራዊ ታሪክ ጉዞ ውስጥ በስኬት የተጠናቀቀው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ኢትዮጵያን ከዘመናት ውጥረትና ከግጭት አዙሪት ወጥታ ወደ ተረጋጋ፣ ስልጡንና አሳታፊ የሀገር ግንባታ ምዕራፍ ለመሸጋገር የምታደርገውን ጥረት የሚያበስር ታሪካዊ ክንውን ሆኖ ተመዝግቧል።

ይኸው ታላቅ ሀገራዊና አህጉራዊ ስኬት፣ ከታሪካዊው የአድዋ ድልና ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ማጠናቀቂያ ምዕራፎች ቀጥሎ፣ ኢትዮጵያውያን የጠብመንጃን መንገድ በመተው በስልጡን የምክክር ባህል አዲስ የታሪክ ዐሻራ ያኖሩበት ታላቅ መድረክ ነው።

የዚህ ታሪካዊ ሂደት ዋና እሴትና መለኪያ ጊዜያዊ የፖለቲካ ማረጋጊያ ወይም የስልጣን ድርድር ስምምነት መፈለግ ሳይሆን፣ ኅብረ-ብሔራዊ ኢትዮጵያዊነት የተንጸባረቀበት፣ እኔነትንና ጠባብ ወገናዊ ፍላጎቶችን ትቶ ሀገር ወዳድነትን ያስቀደመ፣ ለቀጣዩ ትውልድ የሚሻገር ጽኑ ማኅበራዊ ውል ማሰር ነው።

ሀገር በጥቂት ወገኖች የስልጣን ስምምነት ብቻ ሳይሆን፣ በሕዝቦች የጋራ መተጋገዝ፣ በመከባበር፣ በማኅበራዊ ትስስርና በዜጎች እውቀት ውህደት እንደሚገነባ መድረኩ በተግባር አስመስክሯል።

በቅርብ ዓመታት ባጋጠሙ ውስብስብ ፈተናዎች ወቅት የኢትዮጵያ ማኅበራዊ ትስስር ተበጥሷል የሚሉ ተስፋ አስቆራጭ ድምዳሜዎች ሲያንጸባርቁ የቆዩ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያውያን በሺህ ዓመታት የታሪክ ማህፀን ያደለቡትን የዕርቅና የሽምግልና እሴት በመጠቀም የውስጥ ፈተናዎቻቸውን በራሳቸው አቅምና ጥበብ የመሻገር ብቃታቸውን አረጋግጠዋል።

ይህም ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ የማበጀት መርህን በተግባር ያረጋገጠ ሲሆን ኢትዮጵያ በታሪኳ የነፃነት ፋና ወጊ እንደነበረች ሁሉ ዛሬም በሰላማዊ የግጭት አፈታትና በሀገረ-መንግሥት ግንባታ ረገድ ዘመናዊ የአህጉራችን አርአያ መሆኗን አሳይታለች።

ሂደቱም ዜጎች በነፃነት ድምፃቸውን ያሰሙበት፣ የነበሩ ስህተቶች ታርመው መልካም እሴቶች እንዲጎለብቱ ያደረገ ክፍት መድረክ ነበር።

የተከናወኑት ሀገራዊ ውይይቶችና የቀረቡት ምክረ-ሐሳቦች አሁን ላይ ተቀርጸው የሚያበቁ ሳይሆኑ፣ እያደጉና እየበለጸጉ የሚሄዱ የጋራ አሸናፊነት የሚያቀዳጁ ህያው ፍኖተ-ካርታዎች ናቸው።

የዚህ አጠቃላይ ሂደትና የትጋት ውጤት ዋና ዳኛ የኢትዮጵያ ሕዝብ በመሆኑ፣ በምክክሩ የተገኙት አዎንታዊ ምክረ-ሐሳቦች በተቀባይ አካላት ሳይቀዘቅዙ ወደ ተግባር ተለውጠው የኢትዮጵያን እርምጃ ወደ ላቀ ብልፅግና፣ ሰላም እና ዘላቂ መረጋጋት የሚያሻግሩት ይሆናል።

በሰለሞን ገዳ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: