የሀገረ መንግሥት ግንባታ ጉዞ እውነተኛው ስኬት ተቋማት በሚፈጥሩት መዋቅር ወይም በየጊዜው በሚደረጉ የምርጫ ውድድሮች እንዲሁም ማኅበረሰቡ በፈተናዎች እና በጭንቅ ውስጥ በሚያሳየው የንቃተ-ሕሊና ሽግግር ነው።
7ኛዉ ጠቅላላ ምርጫ ከተለመደው የድምፅ አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓት ባሻገር በኢትዮጵያ ምድር አዲስ የምክንያታዊነት እና የማኅበራዊ ውል መሠረት የተጣለበት ክስተት ሆኖ ሊወሰድ ይችላል።
ይህ ምርጫ ዜጎች በውስጣዊ ችግሮች እና በውጫዊ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎች ማዕበል ውስጥ ሆነው የወደፊት ዕጣ ፈንታቸውን በስሜት ሳይሆን በበሰለ ስትራቴጂካዊ ምርጫ የወሰኑበት ታሪክ ምዕራፍ ማሳያ ነው።
የዚህ ሂደት ዋና መገለጫ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአጥፊ እና ከፋፋይ የፖለቲካ ንግግሮች ራሱን በማራቅ ወደ ተግባራዊ እና ዘላቂ የፖለቲካ ባሕል መሸጋገሩ ነው።
ምርጫውን ለማደናቀፍ የቆሙ ኃይሎች የተለያዩ ሙከራዎችን ቢያደርጉም ሕዝቡ መራራ መስዋዕትነት በመክፈል “ሕዝብን ማሸነፍ አይቻልም” የሚለውን ዘላለማዊ እውነት በተግባር አስመስክሯል።
በመሆኑም ሂደቱ የሰላም ወዳዱ ሕዝብ የሞራል የበላይነት የታየበት እንጂ ተራ የፖለቲካ ፉክክር ማሳያ አልነበረም።
የፖለቲካ ፍላጎትን በኃይል እና በጠመንጃ ለመጫን የሚሞክረውን እና የተፈጸሙትን ጥቃቶች በካርዱ ውድቅ ማድረጉ በሀገራችን የፖለቲካ ምህዳር ላይ አዲስና ጸረ-ሁከት አስተሳሰብ መፈጠሩን ያሳያል።
ሕዝቡ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ምርጫዉን ለጸጥታ መታወክ መንስኤ አድርገው ለራሳቸው እኩይ ዓላማ ሊጠቀሙበት እንደነበር በሚገባ ተረድቷል።
ይህ የሕዝቡ ውሳኔ በጠመንጃ የሚመጣ የትኛውም ኃይል የሕዝብን እውነተኛ እና የረጅም ጊዜ ፍላጎት ሊወክል እንደማይችል ለውስጥ እና ውጭ አካላት የተላለፈ ግልጽ መልዕክት ነው።
የዚህ ምርጫ ስልታዊ እና አዲስ መልዕክት ከሀገር ውስጥ የፖለቲካ መረጋጋት አልፎ ከሀገራችን የሉዓላዊነት ክብር እና ከቀጠናዊ ዲፕሎማሲ ጋር በጥብቅ የተሳሰረ መሆኑ ነው።
ጠንካራ እና ሰፊ የሕዝብ ውክልና ያለው መንግሥት መኖሩ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተሰሚነት እና ክብር ያሳድጋል፡፡
በተጨማሪም በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ያላትን ስትራቴጂካዊ ፍላጎት ለማስከበር ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ መሠረት ይጥላል።
በተለይም ታሪካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ተፈጥሯዊ መብት የሆነውን የባሕር በር ተደራሽነትን እና የቀጣናዊ ትስስር ጥያቄዎችን በበሰለ እና በጠንካራ መንገድ ለመደራደር ምርጫው ለሀገራችን አዲስ የሞራልና የፖለቲካ የበላይነት አጎናጽፏታል።
በአጠቃላይ ዘንድሮ የተካሄደው ምርጫ የፈተናዎች ማለፊያ ብቻ ሳይሆን ሕዝቡ በጽናቱ እና በበሰለ ውሳኔው ሀገራችንን ወደ ተሟላ ብልጽግና፣ ሰላም እና ልማት ያሻገረበት አዲስ ታሪካዊ ምዕራፍ ነው።
በበረከት ሽመልስ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: