የአዲስ አበባ ከተማን ታሪካዊ ሰፈሮች አቋርጦ የሚፈስሰው የቀበና ወንዝ፣ ለዘመናት የጠራ የውኃ ምንጭ፣ የህጻናት መዋኛ እንዲሁም የማኅበረሰቡ የዕለት ተዕለት ኑሮ መደገፊያ ሆኖ አገልግሏል።
ድምፃዊ ፀሐዬ ዮሐንስ "የኔታ" በተሰኘው አልበሙ ውስጥ ያካተተው "ቀበና" የተሰኘ ዜማ፣ ይህንን የወንዙን ጥንታዊ ተፈጥሯዊ ውበት እና ማኅበራዊ እሴት በትዝታ እና በቁጭት በጉልህ የሚያስታውስ ነው።
ድምፃዊው በዘፈኑ መክፈቻ ላይ "ቤና... ቤና ሂንዴምና፣ ኦፍ ቀበኔስና... ኤሳ? ቢሻን ቀበና" (እንሂድ እንሂድ፣ ለምን እንቃጠል... የት? ቀበና ወንዝ ወርደን ቀዝቀዝ እንበል) በማለት ወንዙ ለነዋሪዎች የነበረውን ቀጥተኛ ጠቀሜታ እና ማኅበራዊ ጥሪ ያስገነዝባል።
በተለይም ሞቃታማ በሆነው ወቅት ቀዝቀዝ ለማለት የቀበና ወንዝ ፍቱን እንደነበር የልጅነቱን ትዝታ ያነሳበታል።
እንዲሁም "በጋም ሆነ ክረምት በፀሐይ ደመና፣ ከዚያም ከዚያም መጥተን ዋኝተናል ቀበና፤ ምንም ብንራራቅ ቢለያይ ደብራችን፣ ከማዶ እስከ ማዶ አንድ ነው ወንዛችን" በሚሉት ስንኞቹ፤ ወንዙ ከፈረንሳይ ቤላ፣ ከአዋሬ፣ ከሾላ እና ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ታዳጊዎችን ያለ አንዳች የሰፈር ልዩነት በአንድነት የሚያስተሳስር ማኅበራዊ ድልድይ እንደነበር በግሩም ሁኔታ ይገልጻል።
ይሁን እንጂ ይህ የልጅነት ትዝታ ያረፈበት ንጹህ ወንዝ፣ ባለፉት አምስት አሥርት ዓመታት ውስጥ በደረሰበት እጅግ የከፋ ሥነ-ምህዳራዊ ውድመት ምክንያት ወደ አስፈሪ የቆሻሻ መጣያነት ተቀይሮ ቆይቶ ነበር።
የከተማዋ ሕዝብ ቁጥር በፍጥነት መጨመሩን ተከትሎ የተለያዩ ኢንዱስትሪዎች፣ ሆቴሎች እና የመኖሪያ ቤቶች ፈሳሽ ቆሻሻቸውን በቀጥታ ወደ ወንዙ መልቀቅ በመጀመራቸው ወንዙ ክፉኛ ተበከለ።
በዚህም ሳቢያ በውኃው ውስጥ የነበረው የኦክስጅን መጠን በማሽቆልቆሉ ዓሳዎች እና የውኃ ውስጥ ነፍሳት ሙሉ በሙሉ ጠፍተው ወንዙ የበሽታ ምንጭ ሆኖ አለፈ።
ከጥሩ የመዋኛ እና የመዝናኛ ስፍራነት ይልቅ መጥፎ ሽታ ያለው እና ሰዎችን የሚያሸሽ መርዛማ ቀጣና ሆኖ መቆየቱ፣ ዜማው ላይ ለተንጸባረቀው ትዝታ እና የተፈጥሮ መቆርቆር ቁጭት ትልቅ ማሳያ ነው።
ያም ሆኖ ቀበና ቦርቀውበት ካደጉት ከፀሐዬ እና የሱ ዘመን ትውልድ የትዝታ መነጽር ውስጥ እንዳልተፋቀ ፀሐዬ በስንኞቹ ነግሮናል።
ዛሬ ላይ ግን ያ ታሪክ ተቀይሮ፣ የትዝታው ቀበና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አማካኝነት በተሠራው ዘመናዊ የኮሪደር ልማት ታላቅ የከተማ ሐይቅ ሆኖ አስደናቂ ትንሣኤን አግኝቷል።
የቀድሞው የቆሻሻ መጣያ እና የበሽታ ምንጭ አሁን ላይ ውኃው ታክሞ የጸዳበት፣ ማራኪ ሰው ሠራሽ ሐይቅ ወደመሆን ተሸጋግሯል።
በአካባቢው በሺዎች የሚቆጠሩ ሀገር በቀል ዛፎች እና አበቦች በመተከላቸው፣ ወንዙ ዳግም ወፎች የተመለሱበት የአዲስ አበባ አረንጓዴ ሳንባ ሆኗል።
ከእንጦጦ እስከ ካራማራ ድልድይ የተዘረጋው ይህ ልማት የስኬትቦርድ መጫወቻ ስፍራዎችን፣ የልጆች መጫወቻዎችን፣ የብስክሌት መንገዶችን እና ካፌዎችን በማካተት አካባቢውን ወደ ዓለም አቀፍ ደረጃ መዝናኛነት ቀይሮታል።
ይህ ታላቅ የተሃድሶ ሥራ በወንዙ የልጅነት ትዝታ ላላቸው ሰዎች ከማኅበራዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ቁስል መፈወስ ጋር እኩል ነው።
ልማቱ የጠፋውን የሥነ-ምህዳር ትስስር ከመመለስ ባሻገር፣ የሀገር በቀል ዕውቀትን ከዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጋር በማዋሃድ ታሪካዊ የማንነት ትስስርን በዘመናዊ መልኩ ዳግም ማደስ እንደሚቻል በተግባር አሳይቷል።
በዚህ ሂደት አዲስ አበባም ከብክለት እና ከተረሱ የተፈጥሮ ሀብቶች ገጽታ ወጥታ ወደ ዘመናዊ፣ ጽዱ እና ለነዋሪዎቿ ምቹ ወደሆነች ከተማ በፍጥነት እየተለወጠች ነው።
ዛሬ ላይ የቀበና ወንዝ የድምፃዊ ፀሐዬ ዮሐንስ የትዝታ እና የቁጭት ዜማ ብቻ ሆኖ አልቀረም፤ ይልቁንም የነገዋ አዲስ አበባ ህያው የውበት እና የለውጥ ምስክር ሆኖ በድምቀት ቆሟል።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: