በኢትዮጵያ ለቱሪስት መስብነት የታደለችውና የተትረፈረፈ የተፈጥሮ ፀጋ ባለቤት የሆነችው አርባምንጭ ከተማ፣ በሀይቆች፣ በተራሮች፣ በዛፎች እና ደሴቶች ተከባ አረንጓዴ የተላበሰች የተቀናጀ ልማትን ዘርግታለች።
ስሟን እና ታሪኳን አስተሳስሮ በተሠራው በኮሪደር ልማትም ይበልጥ ሳቢና ማራኪ የቱሪስት መዳረሻ ሆናለች።
በከተማዋ በ12 ምድብ ተከፋፍሎ የተሠራው የኮሪደር ልማት ሥራ የሕዝብ መዝናኛ፣ የስፖርት ማዘውተሪያ፣ የገበያ ማዕከላት፣ የህፃናት መጫዋቻ ቦታ፣ የመኪና ማቆሚያዎች እንዲሁም ታሪኳንና ስሟን የሚወክሉ 40/42 እና 63/8 የሚባሉ የደረጃ ፕሮጀክቶችንም አካትቷል።
40/42 የሚለው ስያሜ የተሰጠውም ቱሪስቶችን ወደ አርባዎቹ ምንጮች እና አርባምንጭ ደን የሚወስደው ደረጃ የአርባምንጭ አርባ ምንጮች መገለጫ ሲሆን፣ 42 ደግሞ አርባ ሁለቱን የጋሞ “ደሬዎች” ማለትም ጎሳዎችን የሚወክሉ ናችው።
63/8 ተብሎ የተሰየመው ሌላኛው ፕሮጀክት ደግሞ በ1955 ዓ.ም የተቆረቆረች አርባምንጭ ዛሬ 63 ዓመት መሆኑንና እና 8 ደግሞ ለረጅም ጊዜ የነበረውን የልማት ጥማት ከለውጡ ማግሥት ጀምሮ በርካታ ልማት የተሠራበት በመሆኑ 8 የልማት ዓመታትን ለመግለጽ ታስቦ ነው።
የከተማ ኮሪደር ልማት በተለይ የመንገድ መሠረት ልማት በየአቅጣጫው አንዱ ከአንዱ ጋር የተሳሰረ ሲሆን፣ የአንዱ ሎት (ምድብ) መነሻ ለሌላይኛው ደግሞ መድረሻ ይሆናል።
በዚህም አርባምንጭ ዙሪያዋን የከበቡ ሀይቆች፣ ተራሮች እና አረንጓዴን ለማየት አመቺ ሆኖ እየተሠራ ይገኛል።
ከ50 በላይ የሕዝብ መዝናኛዎች ያለው የአርባምንጭ ኮሪደር ልማት በርካታ የስፖርት ማዘውተሪያ፣ የአካል ጉዳተኞችና እግረኞች ምቹ መንገድ፣ የፐብሊክ ፕላዛዎች እና አንፊ ቴአትር ጨምሮ የተለያዩ የሕዝብ መገልገያዎች ያካተተ ነው።
ከተማዋን በሙሉ በማካለል እየተሠራ የሚገኘው ከ20 ኪሎ ሜትር በላይ የሚረዝመው የኮሪደር ልማት ሥራ አርባምንጭን ይበልጥ የዘመነች እና የቱሪዝም ከተማ አድርጓታል።
በትዕግስቱ ቡቼ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: