Search

የአዲስ አበባን ገጽታ ሙሉ በሙሉ እየቀየረ ያለው “የእንጦጦ - ቀበና የወንዝ እና የወንዝ ዳርቻ ልማት” ፕሮጀክት አስገራሚ ስኬቶች

ሰኞ ሰኔ 22, 2018 214

አዲስ አበባችን በቀን ከሌሊት እያደረገችው ያለችው አስገራሚ የለውጥ ጉዞ አሁን ደግሞ ሌላ አዲስ ታሪክ አስመዝግቧል።

ከተማዋን ወደ ላቀ የሥልጣኔና የውበት ማማ ላይ ካሸጋገሯት ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የሆነው የእንጦጦ - ቀበና የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ግንባታ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ዝግጁ ሆኗል።

ይህ ፕሮጀክት አዲስ አበባ በተግባር እያሳየችው ያለችው ዘመናዊ የከተማ ሽግግር እና የአረንጓዴ ልማት ስኬት ዋነኛ ማሳያ ነው።

በአጠቃላይ 10.5 ኪሎ ሜትር ርዝመት ባለው የውኃ መስመር ላይ ያረፈውና ወደ 87.6 ሄክታር የሚጠጋ መሬትን ያቀፈው ይህ ፕሮጀክት፣ በውስጡ በርካታ ዘመናዊና ማራኪ የሕዝብ መጠቀሚያዎችን ይዟል።

በወንዝ ልማት ዘርፍ አንድ ግዙፍ ግድብ፣ 16 አነስተኛ ግድቦች፣ 3 ቼክ ዳሞች፣ የውኃ ምንጭና 3 ማራኪ ፏፏቴዎች የተገነቡ ሲሆን፣ 20 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያለው የድጋፍ ግንብም ተሠርቷል።

የአፈርና ሥነ-ምሕዳር ጥበቃን ለማረጋገጥ ደግሞ የኮንሶ ጋቢዮንና እርከኖች በስፋት የተገነቡ ሲሆን፣ 59 ሄክታር በላይ መሬት በአረንጓዴ ልማት ተሸፍኖ 50 ሺህ በላይ ውብ ዛፎች ተተክለውበታል።

በተቀናጀ የመሠረተ ልማት ግንባታው ረገድም ፕሮጀክቱ እጅግ አስደናቂ ሲሆን፣ 10 ኪሎ ሜትር በላይ የአስፋልት መንገድ፣ 33 ኪሎ ሜትር የሚረዝም የእግረኛ መሄጃና ዘመናዊ የመንገድ መብራቶች ተዘርግተውለታል።

ከሁሉም በላይ ደግሞ አካባቢውን ውብ ያደረጉ 21 የእግረኛ ድልድዮች ተገንብተዋል።

ነዋሪዎች ዘና የሚሉባቸው 9 የስፖርት ማዘውተሪያዎች፣ 7 የልጆች መጫወቻዎች፣ 4 የመሰብሰቢያ ስፍራዎች፣ 2 አንፊ ቲያትሮች፣ 10 ካፍቴሪያዎች፣ 32 ኪሎ ሜትር የሚሸፍኑ ሱቆችና 2 አነስተኛ የሕዝብ ቤተ-መጻሕፍት ተካተውበታል።

በተጨማሪም 19 ኪሎ ሜትር የፍሳሽ ማስወገጃ፣ 23 መጸዳጃ ቤቶች፣ 7 ፕላዛዎች፣ 4 ፓቪሊዮኖች እና በአንዴ 695 ተሽከርካሪዎችን ማቆም የሚችሉ 7 ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያዎች ተዘጋጅተዋል።

ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት አዲስ አበባችን የምርም የብልጽግና እና የውበት ተምሳሌት እየሆነች ለመምጣቷ ትልቅ ማረጋገጫ ነው።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: