በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ያሸነፈችው ኢትዮጵያ ናት፤ ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ ያደረጉት ደግሞ ሕዝቦቿ ናቸው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
የከተማዋ ነዋሪዎች ምርጫውን ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሃዊና ነፃ ሆኖ በስኬትና በውጤት እንዲጠናቀቅ በማድረጋቸው እና የብልፅግና ፖሊሲና ስትራቴጂ ብሔራዊ ጥቅሞች ያረጋግጣል በማለት ብልፅግና ፓርቲን በአብላጫ ድምፅ በመምረጣቸው ምስጋና አቅርበዋል።
ሀገርን ማፅናት፣ ሰላምን ዘላቂ ማድረግ፣ ብሔራዊ ጥቅሞችን ማረጋገጥ የኢትዮጵያን የመቻል ማሳያዎች መሆናቸውን ከንቲባዋ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ገልጸዋል።
ለበርካታ የሚዲያ ዘመቻዎች፣ ከውጭም ከውስጥም ለነበሩ ጫናዎች ጆሮ ሳትሰጡ የኢትዮጵያን የመቻል አቅም ያረጋገጣችሁ የከተማችን ነዋሪዎችን በፓርቲያችንና በመንግሥታችን ሥም እናመሰግናለንም ነው ያሉት።
ሌሊት ወጥታችሁ ከቴክኖሎጂ መስተጓጎል ጋር በተፈጠረው እንግልት ሳትሰላቹ፣ ቀኑን ሙሉ ደከመኝ ሳትሉ እስከሌሊት በፅናት በመሰለፍ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ እንዲረጋገጥ አድርጋችኋል ሲሉም አክለዋል።
ልማታችን እንዲቀጥል፣ ሰላማችን እንዲረጋገጥ አድርጋችኋል ያሉት ከንቲባ አዳነች፣ ብልፅግናን ስትመርጡ ምንም ችግር የለም ብላችሁ ሳይሆን፣ ያልተመለሱ ጥያቄዎች በሂደት ይመለሳሉ፣ ያልጨረስናቸው ሥራዎች በሂደት ያልቃሉ፣ የጎደለው ይሞላል ብላችሁ እምነት ሰጥታችሁ ነው ብለዋል።
የተሰጠውን አደራም በታማኝነትና በመሰጠት፣ በትጋትና በቁርጠኝነት፣ 24/7 በመሥራት አዲስ አበባን የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: